Thursday, August 23, 2012

ኮንጎ - የጉዞ ማስታወሻ ፪


ከሰሞኑ አንድ ምሽት ላይ ከኪንሻሳ ወጣቶች ጋር የባጥ የቆጡን ሳወጋ ነበር፡፡ እንደአብዛኛው የሀገሪቱ ወጣቶች ሁሉ የአለም መጨረሻው ፈረንሳይ ድምበር ከሚመስላቸው ከእነዚህ ጓደኞቼ አንዱ ታድያ ድንገት በጨዋታው መሃል ስለ ኢትዮጵያ ሲያነሳ ቀልቤን ሰበስቤ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ሲጓዝ በአዲስ አበባ በኩል ትራንዚት አድርጎ እንደነበር እና የአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ በአግራሞት ተናገረ፡፡ እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያ እንዴት እያደገች እንዳለች ለተቀሩት ማስረዳት ቀጠልኩ፡፡

ሶስት ቀናት ሶስት ነገሮች (Aug 23, 2012)

(ባለፉት ሶስት ቀናት እየሁ ሰማሁ ታዘብኩ)

1.      ክፉም ሆነ ደግ፣ ደሃም ሆነ ሃብታም፣ ታሪክ ሰራም አልሰራም፣ ማንም ከሞት አያመልጥም፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ህልፈት አይኑ ያልደረቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም አጣ፡፡ ባዶ ቤት ባዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ባዶ ቤተ መንግስት  . . . ታሪክ ግን ብቻውን ቀረ፡፡ መልካም ስራቸውን እና ጉድለቶቻቸውን ገፅ በገፅ ይዞ ታሪክ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ብቻውን ቀረ፡፡

2.     የስራ ባልደረባዬ ለዚች ሀገር (ዲ.ሪ. ኮንጎ) እንደእኔው እንግዳ ነው፡፡ ብዙ አፍሪካ ሀገሮች ላይ ንግድ ሰርቷል፡፡ እንደ ዲ.ሪ. ኮንጎ አይነት ለቢዝነስ ምቹ ሀገር የትም አይገኝም አለኝ፡፡ ምክንያቱን ስጠይቀው እንዲህ የሚል አስገራሚ መልስ ሰጠኝ "ህግ የሌለበት ሀገር ስለሆነ"፡፡

3.     ሮበን ቫን ፐርሲን የገዛው ትልቁ ማንቸስተር ዩናይትድ ተሸነፈ፡፡ ያስቃልም ያሳዝናልም፡፡

የግድ ነው፡፡ ሶስት ነገሮች ሳይከሰቱ ሶስት ቀኖች አያልፉም፡፡

Monday, August 20, 2012

እኛ እጅ እናወጣለን - እግዚዓብሔር ይመርጣል



ይህችን የጥንት ቤ/ክ ባሰብኩ ቁጥር ልቤን አንዳች ነገር ወደታች ይጫነኛል፡፡ የሀዘን ስሜት ይከበኛል፡፡ የመንግስተ ሰማይ ተምሳሌት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በችግር ተይዛ ስታጣጥር መመልከት እጅግ ያሳምማል፡፡ ለብዙዎች የመፍትሔ ምንጭ የሆነች ቤ/ክ ራሷ ተቸግራ፣ ብዙዎችን ያከመች ቤ/ከ ራሷ ታምማ፣ ታላላቅ ሰዎችን ያፈራች ቤ/ክ ለራሷ የሚሆን ወሳኝ ሰው አጥታ ማየት የእውነትም ይጎዳል፡፡

Wednesday, August 15, 2012

ዜና ነገ ፩


የግብርና ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው ለቀቁ፡፡

ሰኔ 29፣ 2015ዓ.ም (በኢትዮ. አቆጣጠር):- በትላንትናው ዕለት ለተወካዮች ም/ቤት የአመቱን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የግብርና ሚስትሩ የተከበሩ አቶ ብርሃን ባልቻ ሪፖርቱን ባቀረቡ ማግስት ስልጣናቸውን የመልቀቃቸውን ምክንያት ሲገልፁ "ሪፖርቱ ገበሬው በሚገባ ተጠቃሚ እንዳልነበር ያሳያል ስለዚህም የታቀደውን ያህል ልንፈፅም ስላልቻልን በፍቃዳችን ቦታውን ለሌሎች ማስረከብ ይኖርብናል" ሲሉ ለሪፖርተራችን ገልፀ  ል፡፡

የኢትዮጵያ አረጋውያን ከክፍያ ነፃ ሆኑ
ጥቅምት 21 ቀን 2009ዓ.ም (በኢትዮ. አቆጣጠር):- በጡረታ የተገለሉ እና በጦር ሜዳዎች ላይ የተካፈሉ አረጋውያን ከመብራት፣ ውሃ፣ ህክምና እና የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ነፃ መሆናቸውን የሚያበስረው አዋጅ ትላንት ጸደቀ፡፡ ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ አዋጅ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ዜና ነገ - እሺ! መፅሔትን እናዘጋጅ በነበረ ጊዜ በፍቅር እፅፋት የነበረች አነስተኛ አምድ ነች፡፡ በነገይቱ ብሩህ ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት የምመኘውን የምፅፍበት ነፃ ግዛቴ ነው::

Saturday, August 11, 2012

ኮንጎሊዝ - የጉዞ ማስታወሻ


የፓትሪስ ሉሙምባ ሃገር  ዲ.ሪ.ኮንጎ ዋና ከተማ የሆነችው ኪንሻሳ እብድ ያደረበት ቤት እንደመሰለች ይኸው ዛሬም ከንጋት ተገናኝታለች፡፡ ካለፈው ሳትማር፣ ከትላንት ሳትለወጥ ትላንት እንዳየናት ይኸው ዛሬም ከነአደረ ፊቷ ፀሀይ ትሞቃለች፡፡ አንዳንዴ ቤቴ ከቢሮዬ ብዙም ባለመራቁ ደስ ይለኛል፡ ምክንያቱም የዳይመንድ ሃብታቸው እየተዛቀ ወደ ምዕራባውያን የሚጋዝባቸውና የበይ ተመልካች ሆነው ከድህነት ጋር በፍቅር የወደቁ ሰዎችን ለረዥም ሰዐት ማየት ያሳምማልና፡፡ የመኪናውን ግርግር አልፌ ራመድ ራመድ እያልኩ ቢሮዬ ገባሁ፡፡

Thursday, August 9, 2012

ዳግም ትንሳዔ???


የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጤንነት በተመለከተ ባለፉትን አርባ አምስት ቀናት ይዘገቡ የነበሩ ዜናዎች እና ከወዲህ ወዲያ የተሰነዘሩት አስተያየቶች እርስበርሳቸው የተጣረሱ ከመሆናቸው ባሻገር የብዙ ለውጥ ፈላጊዎችን ደም ሞቅ ያደረገ ሁኔታ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ነፃ የመተንፈሻ ሚዲያ ያጣው የኢትዮጵያ ህዝብም በየፊናው ሆኖ የየራሱን ስሜትና ምኞት ባገኘው የማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ መለጠፉን ተያይዞታል፡፡ አንዱ አዋቂ "ጠ/ሚሩ ከሞቱ 2 ሳምንት አለፋቸው" ሲል ሌላኛው አዋቂ ደግሞ "ንጉሳችን በድል አ/አ ገቡ" ይላል፡፡ አንደኛው የዜና አውታር "ጠ/ሚሩ ከጭንቅላት ጋር የተገናኘ ህመም ይዟቸዋል" ሲለን ሌላኛው ከመቅፅበት "የለም እሳቸውን ካልጋ ያስተዋወቀው የቆየ የሆድ ህመማቸው ነው" ይለናል፡፡ በተለይ ፌስቡክ እና ትዊተር ድረ ገፆች የተቻላቸውን ያህል የየሰውን ስሜት ሲያስተጋቡ ከረመዋል፡፡ ከአንዴም ሶስት ጊዜ ህልፈታቸው በደማቅ አራት ነጥቦች ታጅቦ ታውጇል፡፡ ያንኑ ያህል ግዜም ባይኔ በብረቱ አይቻቸዋለሁ በሚመስል ድፍረት "ሰውየው አዲስ አበባ ምኒልክ ቤ/መ ውስጥ ጋቢ ደረብ አድርገው ሶፋቸው ላይ ጋደም ብለው ሲ ኤን ኤን ከፍተው ዘ ኢኮኖሚስትን እያነበቡ አጃ ነገር እየጠጡ ነው" ያለም አልጠፋም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እንደሰከረ ሰው ከመዘላበድ ውጪ አንድም የመንግስት አካል በግልፅ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት ማብራርያ መስጠት አልደፈሩም፡፡