Thursday, August 9, 2012

ዳግም ትንሳዔ???


የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጤንነት በተመለከተ ባለፉትን አርባ አምስት ቀናት ይዘገቡ የነበሩ ዜናዎች እና ከወዲህ ወዲያ የተሰነዘሩት አስተያየቶች እርስበርሳቸው የተጣረሱ ከመሆናቸው ባሻገር የብዙ ለውጥ ፈላጊዎችን ደም ሞቅ ያደረገ ሁኔታ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ነፃ የመተንፈሻ ሚዲያ ያጣው የኢትዮጵያ ህዝብም በየፊናው ሆኖ የየራሱን ስሜትና ምኞት ባገኘው የማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ መለጠፉን ተያይዞታል፡፡ አንዱ አዋቂ "ጠ/ሚሩ ከሞቱ 2 ሳምንት አለፋቸው" ሲል ሌላኛው አዋቂ ደግሞ "ንጉሳችን በድል አ/አ ገቡ" ይላል፡፡ አንደኛው የዜና አውታር "ጠ/ሚሩ ከጭንቅላት ጋር የተገናኘ ህመም ይዟቸዋል" ሲለን ሌላኛው ከመቅፅበት "የለም እሳቸውን ካልጋ ያስተዋወቀው የቆየ የሆድ ህመማቸው ነው" ይለናል፡፡ በተለይ ፌስቡክ እና ትዊተር ድረ ገፆች የተቻላቸውን ያህል የየሰውን ስሜት ሲያስተጋቡ ከረመዋል፡፡ ከአንዴም ሶስት ጊዜ ህልፈታቸው በደማቅ አራት ነጥቦች ታጅቦ ታውጇል፡፡ ያንኑ ያህል ግዜም ባይኔ በብረቱ አይቻቸዋለሁ በሚመስል ድፍረት "ሰውየው አዲስ አበባ ምኒልክ ቤ/መ ውስጥ ጋቢ ደረብ አድርገው ሶፋቸው ላይ ጋደም ብለው ሲ ኤን ኤን ከፍተው ዘ ኢኮኖሚስትን እያነበቡ አጃ ነገር እየጠጡ ነው" ያለም አልጠፋም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እንደሰከረ ሰው ከመዘላበድ ውጪ አንድም የመንግስት አካል በግልፅ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት ማብራርያ መስጠት አልደፈሩም፡፡


ከብዙ ወራቶች በፊት አንድ አንጋፋ የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን አስታውሳለሁ፡፡ ዜናውን ለመዘገብ የቸኮለው(የተንቀዠቀዠው) የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታድያ የሞተውን ሰው አስቀምጦ ያልሞተውን ሌላ ተዋናይ ሞተዋል ብሎ በምስል አስደግፎ ዘገበልን፡፡ ዛሬ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበት ቦታ ሔዶ በህይወት ካሉ ትንፋሻቸውን ቀድቶ ከሌሉም ምስላቸው ቀርፆ ለሚወዳቸውና ለሚወዱት ህዝባቸው እውነቱን የማሳወቅ ግዴታውን መፈፀም "በሊማሊሞ" በኩል የማቋረጥ ያህል ከብዶታል፡፡ በእርግጥ ከኢቲቪ ይሔን ያህል መጠበቅ 85 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብን እንደመሳደብ ሊቆጠርብኝ ይችላል ቢሆንም እውነቱ ግን ህዝባችን በሶስት ወገን ተከፍሎ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያለህ እያለ መሆኑ ነው፡፡

አንደኛው ወገን ለጠ/ሚሩም ሆነ ለተቀሩት ፖለቲከኞች ከፍተኛ ጥላቻን ያሳደረ የሚመስልና ወደ ጠ/ሚሩ "መጣ" የተባለው መልዓከ ሞት በነካ እጁ ሌሎቹንም እንዲጎበኝ የሚማፀኑ ይመስላሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መሀል አንዳንዶቹ ስለመፃፍ፣ መናገር፣ መደራጀት እና ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ መብት የሚታገሉ እንዲሁም በጥቅሉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጥሰት ኢትዮጵያን ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ፀጉሯ ውጧታል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ደቀ መዝሙሮቻቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ የነዚህ ሰዎች አይን እና አፍንጫ ኢሳት ይባላል፡፡

ሌላኛው ወገን ራሱን እንደ ታማኝ ሃይል አድርጎ የቆጠረ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሰዎች ጠ/ሚሩን "እንኳን ሞት ሊደፍራቸው ቀርቶ የፅድቅ ክንፋቸው ብቅ ሊል አንድ ሐሙስ ብቻ ነበር የቀረው" ማለትን ይዳፈራሉ፡፡ የነዚህ ሰዎች የስሜት ህዋሳቶቻቸው ሁሉ ኢቲቪ ነው፡፡ በነሱ አይን የኢትዮጵያ እድገት 11 ከመቶ የሆነው በፀሀፊዋ ስህተት እንጂ እንደውም 110 ከመቶ እንደሚሆን አይጠራጠሩም፡፡ በእነርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ያለአግባብ አይታሰርም አይገረፍም አይገደልም፡፡ ጋዜጠኞች እንደልባቸው ይፅፋሉ ሃሳባቸውን ያንፀባርቃሉ ለዚህም ማስረጃ እንዲሆናቸው በደርግ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባ ከነበረውን ቢክ እስክሪፕቶ ብዛት አሁን በ350 በመቶ እድገት ማሳየቱን ይናገራሉ፡፡ ለእነርሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ድህነት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ጋዜጠኞች ናቸው፡፡

ሶስተኛው ወገን እኔ እና መሰሎቼ የምንገኝበት የሞኞች ማህበር ሲሆን ፖለቲካን ስሙን እንጂ ጥቅም እና ውስብስብነቱን የማናውቅ የፖለቲካ መሃይሞች ነን፡፡ ከመጀመርያው ወገን የማያስማማን ጠ/ሚሩ እንዲሞቱብን አለመፈለጋችን ሲሆን ከሁለተኛው ወገን የሚለየን ደግሞ እኛ የምንኖረው ህዝቦቿ መከራ በሚያስተናግዱባት ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ቤተመንግስት እና ካዛንቺስ የአንድ ፌርማታ ርቀት ብቻ ቢኖራቸውም ህይወት በቤተ መንግስት ውስጥ እና ህይወት በካዛንቺስ የምድርና የሰማይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እኛ የዚህ ሀሳብ ወገንተኞች አምላክ ፍቃዱ ቢሆን የጠ/ሚራችን ጤንነት ተመልሶ፣ አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ፈርሶ፣ ነፃ ምርጫ ተካሒዶ፣ ህዝብ ስልጣን ይዞ፣ ከቂም የነፃና ያልወገነ ችሎት ተቋቁሞ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ከችሎቱ ፊት ቀርበው መልስ ሲሰጡ ማየት እንፈልጋለን፡፡ የፍርዱ ውጤት ምንም እንዲሆን አንጠብቅም፣ አንጠይቅምም ምክንያቱም ለእውነት እና ለፍትህ የቆመ ችሎት ወደድንም ጠላን ሰለእውነት ይፈርዳልና፡፡

ከዚህ ሁሉ ብዥታ በኋላ እግዜር ብሎ እኚህ ሰው በጤንነት ወደ ወንበራቸው ቢመለሱ፣ እንደ እኔ ሃሳብ  ለሁለተኛ ግዜ ከሞት እንደተነሱ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ጊዜ ያልጠበቁት የህዝብ ምላሽ ያገኙት ጠ/ሚ መለስ "ይህን ህዝብ ምን አድርገነው ነው እንዲህ ፊቱን ያዞረብን" እስኪሉ ድረስ በድምፅ መስጫ ኮሮጆ ውስጥ ገድሏቸው ነበር፡፡ ፈጣሪ መቼም ጥበበኛ ነው እንደምንም ከሞቱበት ተነሱ፡፡ አሁን ደግሞ ከትንሳዔያቸው በኋላ ሰባት አመት ሙሉ በቻሉት አቅም ሁሉ ህዝቡን ደጋፊያቸው ለማድረግ ሲጥሩ ከርመው አሁንም ያ "የህዝብ ማዕበል" ሞታቸውን እንዲህ ሲናፍቅላቸው ሲያዩ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

እስከዛው ግን ፈጣሪ ለአልዓዛር እንኳን ያልሰጠውን ሁለተኛ ዕድል ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ሰጥቶ በህይወት እንዲያቆያቸው እመኛለሁ፡፡

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ ኮንጐ )

No comments:

Post a Comment