Monday, July 30, 2012

አጫጭር ትንፋሾች ፪



ድንገት ነቃ፡፡ የተጀቦነበትንም የፍልስፍና ድሪቶ ከላዩ ገፈፍ አድርጎ አይኑን የሚወጋውን ብርሀን ሊቋቋም እየሞከረ አለምን በግርማሞት መንፈስ አያት፡፡ ዙርያ ጥጉንም ሲገረምም አንዳችም ነፍስ ጎኑ የለም ቢሆንም ብዙም አልተደነቀም፡፡ ምክንያቱም የኔ የሚላቸው ነፍሶች ዞረው ለአለም አግዘው ሲያቆስሉት በተደጋጋሚ ታዝቧልና፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ወፋፍራም ግን አጫጭር ትንፋሾች ጉሮሮውን እየቧጠጡት ሳያውቀው እንዲህ የሚል ድምፅ ያወጣው " . . . ይሻለኛል ችጋር፡፡ ከመቶ እጥፍ በላይ ርሃብ ይሻኛል፡፡ ቁርበቴ ገርጥቶ አጥንቶቼ ገጠው ብውል፣ ባድር፣ ብኖር ይሻለኛል፡፡ በቁራሽ እንጀራ እጦት አንጀቴ ተላውሶ በችንጋር አለንጋ ብጠበስ ብቆላ ለእኔ ይሻለኛል፡፡ ጉንጭ ውሃ አጥቼ ምላስ ከትናጋዬ ቢጣበቅ ከንፈሮቼም ደርቀው ኩበትን ቢያስንቁ እመርጣለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ስለ ተስፋ ይሆናል፡፡ ተስፋ አጥቼ ከምኖር አለም ሁሉ ብትቀርብኝ አይጎዳኝም፡፡ ያለ ተስፋ ከመባዘን፣ ሞት የጀግና ዕረፍት ነው ለእኔ፡፡ ተስፋን ከማጣ የምበላው እህል ባጣ እንኳ ግድ አይለኝም እኔ፡፡ ያለ ገንዘብ መኖር እችላለሁ፣ ያለ ተስፋ ግን እስትንፋስ የሌለኝ ደረቅ እንጨት ነኝ፡፡ " ተመልሶ ተጠቅልሎ ተጋደመ እኔም አልቀሰቀስኩትም::


(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ ኮንጐ )

Wednesday, July 25, 2012

ይቅርታ


አጫጭር ትንፋሾች ፩



በተዘበራረቁ ዕውነታዎች፣ በኑሮ ዳገት እና ቁልቁለት፣ በነፍስ አልባ ንጋት እና ጭለማ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ በዚህች አለም ጫጫታ መሀል ድንገት የሚያነቃው ቢኖር የብቸኝነት የጣት ዕሩምታ ብቻ ነው፡፡ ስነ ኑሮ ብቸኝነትን የቂም ጎጆ፣ የበቀልም መንደርደሪያ ይለው ይሆናል እሱ ግን ከዚህ የተለየ ምናልባት የተሸለ ትርጉም ለብቸኝነቱ ይሰጣል፡፡ በብቸኝነቱ ለጊዜውም ቢሆን ከስጋዊ ጭንቀቱ ርቆ በህሊናው ጫካ ይመንናል፡፡ እንጦጦ አናት ላይ ቤቱን እንዳቆመ ጎበዝ በጊዜ አናት ላይ ሆኖ አላፊ አግዳሚውን ይታዘባል፡፡ ውስጡ ዝም ይልና በቅፅበት፣ በአንዳፍታ ብልጭታ መጪ ህይወቱን ይገምታል፣ ያለፈውን ይገመግማል፡፡ ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ እያጣ በሔደ ቁጥር ምኞቶቹም ከጊዜ  ባላነሰ ፍጥነት ሲነጉዱ ያያቸዋል፡፡ የእርሱ አለም ደግሞ ከምኞት ይጀምራል፡፡ ጥሬ ምኞቶቹን ያለገደብ ከመንገድ ዳርም ቢሆን ያጭዳቸዋል እቅዶቹን ወደ ህይወት ለመዘርዘር ግን ጥሬ ምኞቶቹን ዳግም በብቸኝነት ውስጥ ማመንዠክ ይኖርበታል፡፡ "አሊያማ ሳሩን ብቻ እንዳየው በሬ ወይንም ካፍንጫው ጫፍ ርቀት በላይ ማየት እና ማስተዋል እንደተሳነው ጎረምሳ መሆኔ ነው" እያለም ይጨነቃል፡፡ እናም ፍቀዱለት በብቸኝነት አለም ይናውዝ ዘንድ አትከልክሉት፡፡

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ ኮንጐ )

Tuesday, July 24, 2012

ለምን ሀብታም አልሆንኩም?


ከታክሲ ሾፌሩ ጀርባ ሁለት ወጣቶች ተቀምጠው ነበር፡፡ እኔ ከነሱ ኋላ ባለው ወንበር ላይ ሆኜ ስለ መድረሻዬ እንዲሁም አሁን በውል ስለማላስታውሳቸው ነገሮች አሰላስላለሁ፡፡ ከነዚህ ወጣቶች ውስጥ በእኔ ትይዩ ፊት ለፊት ያለው አንደኛው በመደነቅ እና ለማውራት በመቸኮል አይነት ስሜት እየተወራጨ ሲያወራ ሌላኛው ከናፍሮቹን መክደን እንዳለበት እንኳን ረስቶ በትኩረት አፍጥጦ ያዳምጠዋል፡፡ የወሬያቸው ፍሬ ጉዳይ አንድ በቅርብ የሚያውቁት ሰው በማይታመን ፍጥነት እንዴት ሀብታም እንደሆ ነበር፡፡ 

Monday, July 16, 2012

ZUFAN



Dear Readers, This is my first post and i am very delighted to see you here. Today, i would like to present you a graphical expression called "ZUFAN".
Please feel free to comment or share your opinion about it.

Stay blessed