Tuesday, July 24, 2012

ለምን ሀብታም አልሆንኩም?


ከታክሲ ሾፌሩ ጀርባ ሁለት ወጣቶች ተቀምጠው ነበር፡፡ እኔ ከነሱ ኋላ ባለው ወንበር ላይ ሆኜ ስለ መድረሻዬ እንዲሁም አሁን በውል ስለማላስታውሳቸው ነገሮች አሰላስላለሁ፡፡ ከነዚህ ወጣቶች ውስጥ በእኔ ትይዩ ፊት ለፊት ያለው አንደኛው በመደነቅ እና ለማውራት በመቸኮል አይነት ስሜት እየተወራጨ ሲያወራ ሌላኛው ከናፍሮቹን መክደን እንዳለበት እንኳን ረስቶ በትኩረት አፍጥጦ ያዳምጠዋል፡፡ የወሬያቸው ፍሬ ጉዳይ አንድ በቅርብ የሚያውቁት ሰው በማይታመን ፍጥነት እንዴት ሀብታም እንደሆ ነበር፡፡ 

ታሪኩ የሚወራለትን ሰው ባላውቀውም፤ እንዲሁ ግን በቅርብ ርቀት አዳምጣቸዋለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ መውረጃዬ ሲቃረብ ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ የተናገረው  ሳልፈልግ ውስጤን በጥያቄ አናጋው፤ የደሜን ዙረት ፍጥነት ጨመረው፡፡ “ . . . እኔም ከእርሱ ባልተናነሰ እለፋለሁ እደክማለሁ ታድያ ለምን ሀብታም አልሆንኩም?” ሲል ነበር ሳያውቀው የብዙ ሰዎችን ጥያቄ ያነሳው፡፡ ስንቶቻችንን ይህ ጥያቄ እንደሚመለከተን በቁጥር ማስቀመጥ ባልችልም የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ ግን በርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡
            እንለፋለን፣ እንሰራለን፣ ከፀሀይ ውጣት እስከ ፀሀይ ግባት ያለማቋረጥ እንሮጣለን . . . ታዲያ ለምን እንደምንፈልገው ሀብታም አንሆንም? እስኪ ይህን ጥያቄ ለጊዜው አነሰም በዛም የራሳቸውን ንግድ ወደሚያስተዳድሩ ሰዎች እናዙረው፡፡ በርግጥ በነዋይ የበለፀጉ ለመሆን መስራትና ያለማቋረጥ መልፋት ብቻውን ውጤት ያመጣል?
            እኔ ስራን በተሳካ ሁኔታ ሰርቶ በገንዘብ ሀብታም ለመሆን አስቀድመን ስለምንሰራው ነገር ጠንቅቀን ማወቅ እና ለስራችንም “መሰጠት” ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ የተለያዩ የስነልቦና እንዲሁም የንግድ መፃህፍት የሚጠቁሟቸው ስራን ማሳኪያ መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህ መሀከል ግን አራቱን ብቻ ለይተን በማጉላት በታክሲው ውስጥ ጥያቄውን በምሬት ለገለፀው ወጣት እንዲሁም ለሚመለከታቸው ሁሉ ለምን ሀብታም እንዳልሆንን ለማሳየት እወዳለሁ፡፡
ሀሳብ / Idea
ልንሰራው የምናቅደው ነገር ተቀባይነቱ፣ ተግባራዊነቱ እንዲሁም ልዩነቱ ቀድሞ መጠናት ያለበት የመጀመሪያው ስራችን ነው፡፡ ቀድሞ ገበያ ውስጥ ያለ፣ የተነገረ፣ የተሰማ፣ የነበረን ነገር ያለምንም ለውጥ ይዘን ወደ ገበያ ብንገባ ተቀባነታችን ከምናስበው በታች ይሆናል፡፡ ለደንበኞቻችን አዲስ ነገርን ይዘን መቅረብ ካልቻልን፤ አሊያም ደግሞ ከዚህ በፊት ባልተሞከረ የሽያጭ መንገድ መሸጥ ካልጀመርን ብንደክም ብንለፋ እንዴት ሀብታም እንሆናለን?
ዕቅድ / Plan
ስራችን የተስተካከለ እንዲሆን ከምንም ነገር በላይ ዕቅድ ያስፈልገናል፡፡ ምን? መቼ? የት? እንዴት? እና ማን? የሚሉት ጥያቄዎች ቀድመው መመለስና በወረቀት ላይ መስፈር ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ የንግድ ሰው የትኛውም ቀላል ተግባር ያለ ዕቅድ አይሰራም፡፡ አላማችን በስራ ስኬታማ መሆን እና በገንዘብ መበልፀግ እስከሆነ ተደጋጋሚ ስህተትቶችን የምንቀበልበት አቅም አይኖረንም ምክንቱም ስህተት ወጪ አለውና፡፡ ዕቅድን መከታተል እና መገምገም አብረው ካልሔዱም ማቀድ ብቻውንም እንዲሁ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ታድያ ያለ ዕቅድ ካልተመራን፣ ቀኑ እኛን እንደሚፈልገን ሳይሆን እኛ ቀናችንን እንደምንፈልገው ካልተጠቀምበት ብንደክም ብንለፋ እንዴት ሀብታም እንሆናለን?
የስራ ፍቅር / Dedication
የማይወዱትን ስራ እየሰሩ ስኬታማ መሆን በጭራሽ የማይታለም ነው፡፡ በምትኩ ደግሞ የነፍስ ጥሪያቸውን አዳምጠው ለሚሰሩት ስራ ራሳቸውን በመስጠት በጥንካሬ የሚጓዙ ሁሉ የሚገጥማቸውን ፈተና በቀላሉ በመቋቋም አላማቸውን ማሳካት ይቻላቸዋል፡፡ ያለዚያማ ባልፈለግነው ስራ ተጠምደን ቀኖቻችንን በመሰላቸት እያሳለፍን ብንደክም ብንለፋ እንዴት ሀብታም እንሆናለን?
ቁጠባ / Saving
አሁን ለደንበኞቻችን አዳዲስ ነገሮችን እያቀረብን እኛም በሚገባ በዕቅድ እየተመራን ነው፡፡ ተጨማሪ ደንበኞችና ብዙ ገንዘብም ቀስ በቀስ እየመጣ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ገንዘብ የሚጠራቀመው ገንዘብ የመጣ ጊዜ ነው” ይላሉ፡፡ ገንዘብ መቆጠብ የሚጀመረው እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ ብቻ አይደለም፡፡ ስራ ለመስራትና የገንዘብ ሀብታም ለመሆን ማሰብ ስንጀምር ጀምሮ መቆጠብን ማወቅ ይኖርብናል ምክንያቱም የገንዘብ ትንሽ የለውምና፡፡ ካልሆነማ በብዙ ውጣ ውረድ የምናገኘውን ደቃቅ ሳንቲሞች በቀላሉ ካባከንን እንዲሁ ብንደክም ብንለፋ እንዴት ሀብታም እንሆናለን?

. . . ሰላም::
Alemayehu A. Kidane
(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ ኮንጐ )

2 comments:

  1. I didn't know that you are such a great writer. I am really liking it. You are using your real talent. Great keep it up.

    ReplyDelete