Friday, October 5, 2012

እኔ እግዚአብሔር እና ስሜ



በጭለማው መሃል ድንገት ተስፈንጥሮ ተነሳና ማብሪያ ማጥፊያውን ተጭኖ ጭለማውን ገሰሰው፡፡ አናቴ ደንግጣ እያማተበች በዚያ ለሊት የሚያፈጥባትን ሰውዬ መልሳ ትመለከተዋለች፡፡ “ምንድነው ይሔ?” አላት ሆዷን በሌባ ጣቱ እየጠነቆለ፡፡ እንደመተንፈስ አለችና “እኔንጃ” አለች ፊቱን ላለማየት አቀርቅራ፡፡ “እኔንጃ? ምንማለት ነው እኔንጃ? ኪኒን እንድትወስጂ ተስማምተን እየዋጥሽ አልነበር እንዴ?” በዚያ ፀጥ ባለ ሌሊት የእርሱ ድምፅ ብቻውን እንደመብረቅ ይጮሃል፡፡ “አዎ ኪኒኑንማ እየዋጥኩ ነው” አሁንም እንዳቀረቀረች ነው፡፡ “እና?!?!?” በይበልጥ አምባረቀ፡፡ ከዚህ በላይ መታገስ የምትችል አልመስል አላት ቢመታትም ጠንካራ ክንዱን ለመቻል ተዘጋጅታ “እንግዲህ ኪኒኑ አልሰራልኝም ማለት ነው ያለዚያማ እንዴት ልፀንስ እችላለሁ?” አለችው ተኮሳትራ፡፡ እንግዲህም ይህ ቅፅበት ነበር ለእኔ የህይወት መጀመርያ ለወላጆቼ ደግሞ የመጨረሻዋ ቀን የሆነችው፡፡ አቶ “አባት” እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ የሰውና የጊዜ ክፉ የገጠማት እናቴም እኔን በሆዷ የሆነውን ሁሉ በልቧ ይዛ ብቸኛ ሆነች፡፡ አላማዬ የህይወት ታሪኬን ልነግራችሁ አይደለም የስሜን አመጣጥ ለማብራራት ይሔን ታሪክ መንገር ስላስፈለገኝ እንጂ፡፡

እናቴ እትብቴን እና ምስጢሯን አፈር ካስገባች በኋላ “አለምዓየሁ አጥናፍሰገድ” የሚል ስም ሰጠችኝ (ሰውየውን በመሔድህ አለም ነው ያየሁት ስትለው)፡፡ ባለበት ሆኖ ይህን የሰማው ሰውዬ ደግሞ “አይገኝ አጥናፍሰገድ” አለኝ (ለእናቴ እኔ አጥናፍሰገድን ብትፈልጊኝም አታገኚኝም ለማለት ፈልጎ)፡፡ ብላቴናው እኔ በሁለት ስም መሃል በስለት ከተወለዱ ልጆች እኩል አደግኩና ነፍስ አወቅኩኝ፡፡ አስር፣ አስራስምንንት፣ ሀያ እና ሀያ አምስት ዕድሜንም አለፍኩኝ፡፡

አንድ ቀን ታድያ ይሔን የወላጆቼን የስም ጦርነት ማቆም ፈልጌ የራሴን ስም በራሴ ማውጣት ወሰንኩኝ፡፡ ነገር ግን አዲስ የስም አማራጭ ከመፈለጌ በፊት እነዚህን ሁለት ስሞች ለማንም ሳላዳላ በጥልቀት መመርመር አስፈለገኝ፡፡ “አይገኝ” የሚለው ስም ከስምነት ይልቅ ለዓረፍተነገርነት ይቀርባል በዚያ ላይ ለእኔ የተሰጠ ሳይሆን ሰውየው ራሱን ለማሞካሸት ያወጣው በመሆኑ ከምርጫዬ ወደቀ፡፡ “አለምዓየሁ አጥናፍሰገድ” የሚለውን ስምም እንዲሁ ከምርጫ ከማስወጣቴ በፊት ሙሉ ስሜን እስከ ቅድመ አያቴ ፅፌ ማገናዘብ ጀመርኩ፡፡  ነገር ግን አለምን ዓየሁ ከሚል ትርጉም በቀር ከህይወቴ ጋር ሊገናኝ የሚችል አንዳች ትርጉም ካለው በሚል እንደ ጅል ሳብላላው ሰንብቼ ውሳኔ ላይ ሳልደርስ በአጋጣሚ ተጋብዤ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ ወደምትገኘው ደብር ቅዱስ ደብረ ፅጌ ማርያም ገዳም ለመሔድ ጉዞ ጀመርኩ፡፡

በምንጓዝበት መኪና ውስጥ አንድ ወጣት መርጌታ ተዋወቅኩኝ፡፡ በጨዋታችን መሀልም ታድያ ስለምንሔድበት ገዳም ማብራርያ ከሰጡኝ በኋላ ድንገት ያልጠበቅኩትን ጥያቄ እንዲህ ሲሉ ጠየቁኝ “የስምህ ትርጓሜ ምን ማለት ነው”፡፡ እጅግ ነበር የደነገጥኩት ምክንያቱም ሲጀመር ስሜን ገና ሳልነግራቸው ትርጓሜውን ስለጠየቁኝ እና ራሴን በራሴ ስጠይቅ የነበረውን ጥያቅ ስለደገሙት ነበር፡፡ ብቻ ምን ልበላችሁ ሰውነቴን የሆነ ነገር ሲወርረኝ ተሰማኝ፣ ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚባለው ተረት ለእኔ እንዳልሰራ ተገነዘብኩ፡፡ ስሜን ከመላዕክ ይልቅ እግዚዓብሔር ራሱ እንዳወጣልኝ በድንገት በዛች አጋጣሚ ሳውቅ የወንድ ለቅሶ አለቀስኩ፡፡ ለካንስ እንዲህ የሚል ስም ይዤ ኖሯል የምንገላወደው አለማየሁ(አለምን ዓየሁ) አጥናፍሰገድ(ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ሲሰግድ) ኪዳኔ(ኪዳን፡- የቃልኪዳን ታቦት) ወልደመድህን (ወልድ ክርስቶስ መድሃኒት)፡፡ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ አለም ሁሉ መድሃኒት ለሆነው ወልድ ክርስቶስ ሲሰግድ አየሁ፡፡ ከዚህ በላይ የምለው የለኝም፡፡ ሰላም ሰንብቱልኝ፡፡

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ.ኮንጎ)

4 comments:

  1. Unbelievable! Is the story at the beginning true? any ways i will check it with Etiye. I didn't know the meaning in such lovely way. More interesting thing is that "U CAN WRITE TRULY". THANK YOU ALEXI

    ReplyDelete
  2. The story from beginning to end is true and sure you can confirm it with Eteye. ነገሩ ይገርመኝ ነበር እንደው ጊዜ ስላጣሁ እና የመፃፍ ችሎታ ስለሌለኝ ታሪኩን እንዳላበላሸው ብዬ ነበር ዝም ያልኩት አሁን ግን በቃ ባሉኝ ቃላት ልጨማለቅበት ብዬ ነው፡፡ ስለወደድከው ደስ ብሎኛል፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. ZE yegerim neger new. Khulum sem jerba, asgerami tarik ale (kene sim besteker):)

      Delete
  3. አዬ ፋሆሎጂስት! ምነው እንደድሮው ባለማወቅ/ባለመተዋወቅ ፈጣሪ የሠጠኝን ዕድሜዬን አጣጥሜ ወደፈቀደልኝ ቦታ በወሰደኝ።
    ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ይሉ ነበር አባቶቻችን::
    ይሄን ጽሑፍ ገና ትናንትና ማየቴ ነው። ታዲያ እንደመብረቅ ነው የመታኝ። በብዙ መሥመሮችም ነው የተመለክትኩት። አሁን፦ በመጠኑም ቢሆን፦ ገባኝ ፣ ሌላ ቀርቶ፣ መቸም ከአንድ እናት ከአንድ አባት መውጣትን መካድ አይቻልምና፤ እኔ ብሆን ምን አደርግ ነበር? (አስተዳደግ ከዕድሜ መጠን በስተቀር አንድ ነበርና) እስከማለት ሁሉ ባለፉት 24 ሰዓታት አዕምሮዬ ሲታገል ውሎ አድሮ ይሄው ይሄንን መልዕክት ለማድረስም ደርሷል።
    ከዚህ ሁሉ የኔ ትካዜና ሐዘን በኋላ ግን ላካፍልህ የፈለግሁት አንድ ነገር ቢኖር፦ የሰው ልጅ ምንም ዓይነት በደል ቢሰማው (በደል ጥቃት ነውና)፣ ጥቃት ተሸናፊነትን ቢያመለክትም፤ ክርስቶስ እራሱ ያስተማረን ‘ይቅር’ ማለት ድሉን መልሶ ለይቅር ባዩ እንደሚያጎናጽፈውና አንዱ በአንዱ ከመፍረድ እንዲገታ ነው። ይቅር ማለት የራስን መንፈሥ እና ልቦና ከዘላለማዊ እሥራት መፍታት ማለት ነው።

    ለኔ የቀረልኝ ሕመም ግን ከዚህ ጽሑፍህ በኋላ ማን ብዬ እንደምጠራህ ያለማወቄ ነው።

    የቡልጋው ይመኩ ታምራት

    ReplyDelete