Thursday, November 1, 2012

አከራዮቼ 1



እንደው መታደል ሆኖ ከኢትዮጵያዊ እናት ተፈጠርኩኝ እንጂ ወላጆቼ ፈርዶባቸው ፈረንጅ ቢሆኑ ኖሮ እድሜዬ ለአቅመ ሸክም በደረሰ በዚያ ወቅት (በ19 ዓመቴ ማለት ነው) “ሌላ ቤት ተከራይ አሊያም ኪራይ ክፈል” ይሉኝ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ግን እኔ ራሴን መቻል ያሰኘኝ ወቅት ስለነበር እናቴን ሔጄ "ራሴን አሸክሚኝ" ስላት አንድ ቃል ነበር ከአፏ የወጣው “አትቅበጥ” የሚል፡፡ አዲስ ቦታ፣ አዲስ ሰው፣ አዲስ ነገር ሁሉ ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ነገር ወይንም አንድ ቦታ ላይ ችክ ማለት አልችልበትም፡፡ ስልቹ ነገር ነኝ፡፡ የምሰራበት ቦታ ላይ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ካልቻልኩ ቀኑን መግፋት ያቅተኛል፡፡ ተደጋጋሚ(Routine) ነገሮችን እንደመፈፀም የሚያሳምመኝ ነገር እስካሁን የለም፡፡ ለነገሩ ስራ ላይ ብቻ ሳይሆን ቤት ኪራይ ላይም እንዲሁ ነኝ፡፡ ባለፉት በአስር አመታት ውስጥ እንኳን ስምንት ቤቶችን ለዋውጫለሁ፡፡ ኪራይ እስከሆነ ድረስ ምን አንድ ቦታ ላይ አስቸከለኝ?

አንድ ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ከቆየሁ ምክንያቱ የአከራዮቼ ጥሩነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ኪራይ የጀመርኩት ቄራ ጎፋ ማዞርያ አካባቢ ደከም ባለ ቤት ነበር፡፡ ቤቱ ውስጥ የነበረኝ ዕቃ አንድ ፍራሽ፣ አንድ ሲዲ ማጫወቻ እና አንድ የዋይት ሆርስ ባዶ ጠርሙስ ብቻ ነበር (ጠርሙሷ በእርግጠኝነት ከሶማሌላንድ የላቀ ታሪክ ይኖራታል ብዬ አስባለሁ)፡፡ አከራዬ ሴትዮ ከአንድ ትንሽ ልጃቸው ጋር ብቻ ነበር የሚኖሩት - እንደ መጀመርያ ቤቴ ብዙም ከአከራይ ጋር ለመግባባት ባልችልም የባልቴቷና የልጃቸው ጭቅጭቅ በየቀኑ የጭቃ ግድግዳውን እያለፈ ያዝናናኝ ነበር፡፡ አንድ እሁድ ጠዋት ከጓደኛዬ ጋር አርፍደን ተኝተን ሳለ በሩ ተንኳኳ፡፡ እየተጨናበስኩ ከነቁምጣዬ ሔጄ በሩን ከፈትኩ፡፡ አከራዬ በቀኝ እጃቸው የሸክላ ገል ላይ የሚጨስ ነገር እንደያዙ ፍቃዴን ሳይጠይቁ ዘው ብለው ገቡ፡፡ እየተካሔደ ያለውን ነገር ማመን ስላቃተኝ ደነገጥኩ፡፡ “ጭሱ እስኪያልቅ እንዳትነካው” ብለውኝ መልሴን ሳይጠብቁ ውልቅ ብለው ወጡ፡፡ አኳኋናቸው ሁሉ ከሃሪፖተር ፊልም የተቀነጨበ ነበር የሚመስለው፡፡ በሩን ጠርቅሜ ወደ ፍራሼ ተመለስኩ ነገር ግን ያን ቀን ከዛች ፍራሽ ላይ ተላቆ መነሳት አቃተን፡፡ እንዲሁ በጭሱ ታፍነን ስናቃስት/ስንገላበጥ ውለን ከቀኑ አስር ሰዓት ሲሆን እንደምንም እላያችን የሰፈረውን ጂኒ አሸንፈን ተነሳን፡፡ ኋላ ላይ ሳጣራ ሴትየዋ ውቃቢ እንዳለባቸው እና ሃሙስ ሃሙስ ማታ በነጩ ፈረስ እንደሚጋልቡ ሰማሁ፡፡ ለተከታታይ አስር ቀናት ወደዛ ቤት ድርሽ ሳልል ቀርቼ በሚቀጥለው ቀን ስሔድ የበሩ ቁልፍ ከላዩ ተነስቶ ደረስኩ ወደ ክፍሌ ስዘልቅ ህልም የሚመስል ነገር ገጠመኝ፡፡ በአንደኛው ጥግ ላይ ወደ ሃያ የሚሆኑ ጥቋቁር ዶሮዎች ተከማችተው ይንጫጫሉ፡፡ ካሉኝ ሶስት ንብረቶች ሲዲ ማጫወቻው እና ጠርሙሱ ብቻ በሌላ ጥግ ተቀምጠዋል፡፡ እንደምንም ፍርሃቴን ውጬ አከራይቷ ጋር ገባሁ እና ቤቱን ለመልቀቅ እንደመጣሁ ነግሬያቸው “ፍራሼ . . .” ብዬ ልቀጥል ስል ከአፌ ነጥቀው “አንተ ተመስገን! ተመስገን! ተነስ ልጁ መጥቷል ፍራሹን ስጠው” ብለው አስደነገጡኝ፡፡ እዚሀ ቤት ያመጣኝን ደላላ እየረገምኩ፣ ሴትየዋ በርትተው የሀሙስ ቡና አፍይ ሳያደርጉኝ በፊት ያዳነኝን አምላኬን እያመሰገንኩ ከዚያ ሰፈር ለአንዴና ከመጨረሻ ጊዜ ጠፋሁ፡፡

ብዙም ሳልቆይ ቡልጋርያ ማዞርያ አካባቢ አሪፍ ሙስሊሞች ቤት ውስጥ ከባጃጅ የጠበበ ከምስጢር ኪስ የሰፋ ክፍል አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ቤት ያመጣኝ ደላላ "አልጋ አለህ እንዴ?" ብሎ የምሩን ጠይቆኝ ነበር በጣም ገርሞኝ "እንዴ! ምን ማለትህ ነው?" ስለው "አይ አልጋ ካለህ ቤቱ አይሆንህም ብዬ ነው" ሲለኝ ሊያሳየኝ ያልፈለገ መስሎኝ በሽቄበት ነበር ቤቱን ካየሁት በኋላ ግን የአከራዮቹን ድፍረት ከማድነቅ ውጪ አማራጭ ስላልነበረኝ ተስማማሁ፡፡ ምንም ሳላጋንን ካወራሁ እዚህ ቤት ውስጥ ከመቆም የተሻለ የሚመች ነገር አልነበረም፡፡ እንደውም ያን ሰሞን ከጓደኞቼ ስለያይ በሉ እንግዲህ ደክሞኛል እቤት ገብቼ ትንሽ ልቁም ማለት ጀምሬ ነበር፡፡ የቤቱ ባለቤቶች አምስት ልጆች ሲኖሩዋቸው አንዱ ልጃቸው ሲበዛ ብልሹ ነበር (ባለፈው ጊዜ አንድ አዛውንት ሰውዬ ስንት ልጆች አልዎት ተብለው ሲጠየቁ ሶስት ነበሩ ሁለቱ ገሙብኝ ያሉትን ሰምታችኋል እኔ ግን ሳስበው ምናልባት ሰውየው የእንቁላል ፋብሪካ ሰፈር ሰው ሳይሆኑ አይቀርም)፡፡ ግቢው ሰላማዊ ቢሆንም የልጃቸውን ዝርፊያ ግን ሰላሜን ነሳኝ በተለይ ኦሪጅናል ሲዲዎቼን ጨረሰብኝ፡፡ ታግሼው ብኖርም ከቀን ቀን ቤቷ እያነሰች እኔ ደግሞ እያደግኩ፣ የመንጠራራት ፍላጎቴ እንዲሁም የጓደኞቼ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ሳልቀያየም በፊት “ዘመድ Friendly” የሆነ ሰፋ ያለ ቤት መፈለግ ግድ ሆነብኝ፡፡ ለነገሩ የቄራ ሜክሲኮ ሰፈርም ሰልቸቶኝ ስለነበረ ጉዞዬን ወደ ሃያ ሁለት ማዞርያ አደረግኩ፡፡

ይቀጥላል
(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ. ኮንጎ

2 comments:

  1. Enjoyed reading your article. Hope at last you found your dream home.

    London

    ReplyDelete
  2. ባክህ የኔዉ ቢጤ ነክ............እስቲ አጋጭተን ቤት እንስራ!!

    ReplyDelete