Monday, September 16, 2013

አቦነሽ አድነው “አርቲስት” የሚለው መጠርያ ይገባታል?



ቀደም ሲል በተለየ ቅላፄዋና በባህል ሙዚቃዎቿ የምናውቃት አቦነሽ አድነው “ከዚህ በኋላ ዓለም ከአንደበቴ በሚወጣ ዘፈን አትደንስም ይልቁንስ ጩኸቴ፣ ቅኔ እና ዜማዬ የምስጋና ብቻ ነው” ብላ አዲስ የመዝሙር ስራዎቿን ይዛ ሰሞኑን ብቅ ማለቷ የሚመለከታቸውን ሰዎች ሁሉ ሲያነጋግር የሰነበተ ጉዳይ ነበር፡፡ መቼም ሰው ከአካባቢ ተፅንዖ፣ ከዓለም ዳንኪራ፣ ከከንቱ ውዳሴና ጭብጨባ አምልጦ  ሁለመናን ለፈጣሪ ሲሰጥ ማየት መንፈሳዊ ቅንዓት ከማሳደሩም በላይ ያበረታል፡፡ ይህን ስል ግን ዓላማዬ ያልተገባ የሰው ምስጋና ለአቦነሽ ለመስጠት ወይንም ብላቴናዋን ዘማሪት “ቅድስት” ብሎ ለመጥራት አይደለም፡፡
ባለፈው እሁድ ጠዋት አንድ ነጭ ሚኒባስ አናቱ ላይ በተሸከመው ድምፅ ማጉያ አዲሱን የዘማሪት አቦነሽ አድነውን መዝሙር ከፍቶ እያስተዋወቀና ካሴቱን እየሸጠ ነበር፡፡ በመዝሙሩ መሃል ጣልቃ እየገባ አላፊ አግዳሚው ካሴቱን እንዲገዛ የሚያስተዋውቀው ወጣት ታዲያ በተደጋጋሚ “ . . . የአርቲስት ዘማሪት አቦነሽ አድነው  . . .” እያለ ይናገር ነበር፡፡ አባባሉ ለጆሮዬ እንግዳ ሆነብኝ፡፡ በስህተት ነው ብዬ ላልፍ ስል አሁንም በድጋሚ “ . . . የአርቲስት ዘማሪት . . .” እያለ ዘማሪቷን ማስተዋወቅ ቀጠለ፡፡ እኔም ቅር እያለኝ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ታድያ ስለዚያ ካሴት ሻጭ ወጣት ስህተት እያሰብኩ ታክሲ ውስጥ ስገባ መስታወቱ ላይ የዘማሪቷ ምስል ያለበት ፖስተር ተለጥፎ አየሁ ጠጋ ብዬ ሳነበው ስህተቱ የዚያ ወጣት ልጅ ብቻ አለመሆኑን ተረዳሁ፡፡ ፖስተሯም ላይ “የአርቲስት ዘማሪት አቦነሽ አድነው” የሚል ነገር አየሁ፡፡ ያኔ ይህን ነገር እንደስህተት ያየሁት እኔ ብቻ ልሆን እችላለሁ ምናልባትም ስህተት ላይሆን ይችላል የሚል ሀሳብ መጣብኝ፡፡ ዘማሪቷ ራሷ ሀጥያት ነው ባለችውና የአሁን ማንነቷን በማይገልፀው ዘፋኝነቷ ያገኘችውን “አርቲስት” የሚለውን ማዕረግ “ዘማሪት” ከሚለው ጋር አዳብሎ መጥራት ይቻል ይሆን ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ የጠለቀ የሃይማኖት እውቀት የለኝምና፡፡

ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ከሁሉ በፊት አርቲስት በሚለው ቃል እና ዘማሪት በሚለው ቃል መካከል ያለውን ልዩነት እንደባለሙያ ሳይሆን እንደተራ ምዕመን መለየትና መተርጎም ያለብን ይመስለኛ፡፡ እኔ አንድን ሰው አርቲስት ብዬ የምጠራው በስነ ጥበብ ውስጥ ያለ ሰው ሆኖ የተለየ ችሎታ ያለው ወይንም ያላትን ነው፡፡ ለምሳሌ ቀራፂ፣ ሰዓሊ፣ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ዘፋኝ እና የመሳሰሉት ሰዎች አርቲስት የሚለውን የማዕረግ ስም የሚይዙ ሰዎች ሲሆኑ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አገልጋይ፣ ዲያቆን፣ መርጌታ፣ ቄስ፣ መነኩሴ፣ መምህር ዘማሪ እና ሌሎች ስሞች እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ የቀባቸውን ሰዎች የምንጠራበት መንፈሳዊ ስሞች ናቸው፡፡

በአለማዊው ወገን ለምሳሌ አንድ ሰው በጦር ሰራዊት ውስጥ የሰራው ስራ ታይቶና ተመዝኖ ላደረገው ተጋድሎ እንደ ምስጋና ወይንም እንደክብር ተቆጥሮ ኮለኔል የሚል ማዕረግ ሊሰጠው ይችላል ያ ሰው በጡረታ ቢገለል እንኳ የማዕረግ ስሙ እንዳለ ይቀጥላል፡፡ በመንፈሳዊው ዓለው በኩል ደግሞ አንድ አባት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲሾሙ ብፁዕ ወቅዱስ የሚል ማዕረግ ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ሊቀ ጳጳሱ በማንኛውም ምክንያት በምርጫም ሆነ በእርጅና ከተሰጣቸው ሀላፊነት ቢወርዱ ብፁዕ ወቅዱስ የሚለውን ማዕረግ ይዘው አይቀሩም ምክንያቱም ብፁዕ ወቅዱስ የሚያሰኘው የሃላፊነት ቦታው እንጂ በቦታው የነበረው ሰው አይደለምና፡፡

አቦነሽ አድነውን አርቲስት ብለን የጠራናት በዘፈነቻቸው ዘፈኖች ባቀነቀነቻቸው አለማዊ ውዳሴዎች አማካኝነት በመሸታ ቤቶች ውስጥ እና በዳንኪራ መድረኮች ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እርሷ ደግሞ እኔ ከዚህ በኋላ ያ ሰው አይደለሁም ብላናለች፡፡ ይህ ከሆነ ታድያ አቦነሽ አድነውን ከዘፋኝነት መድረኩ ለዘለዓለሙ ከወረደች በኋላ ስለምን አርቲስት ተብላ ትጠራለች? አቦነሽ አድነው ክብሬ እግዚዓብሔር ነው ሌላ ክብርም አልፈልግም ብላለቸና ዘማሪት ብቻ እንጂ አርቲስት እንዴት ትባላለች?
ይህ ነገር ስህተት ካልሆነ እሰየው፡፡ ስህተት ሆኖ ቢገኝም ግን ሃላፊነቱ የማን እንደሆነ አላውቅም፣ በእርሷም ሆነ በዙርያዋ ባሉ ሰዎች ላይ ጣቴን ለመቀሰርም አይደለም፡፡ ምናልባት ግን እርሷን ያልተረዱ ሰዎች ካሴቷን ለመሸጥ ሲሉ ብቻ ታዋቂነቷን መጠቀሚያ እያደረጓት ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት አለኝ፡፡ በመጨረሻ ልንረዳው የሚገባን አንድ ትልቅ ነጥብ ያለም ይመስለኛል፡፡ ዝማሬ አብረን የምናቀርበው ፀሎት፣ መስዋዕት እንዲሁም ምስጋና ነው፡፡ ታድያ ታዋቂ ሰው የዘመረው ታዋቂ ካልሆነው ቀድሞ እግዚዓብሔር ጋር አይደርስም ማንም ይዘምረው ማን ዋናው ነጥቡ ለማን ተዘመረ የሚለው ነው፡፡ ዘማሪት አቦነሽ አድነውም ቀድማ ተስፋ ያደረገችው እግዚዓብሔር ሳይጥላት እስከመጨረሻው በምስጋና ብቻ እንደሚያዘልቃት በእግዚያብሔር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ?

ስ-6-2006

1 comment:

  1. ቅር ያሰኘን ነገር ተስተካክሎ ስህተቱ ታርሞ አርቲስት የሚለው ቃል የሌለበት አዲስ ማስታወቂያ አትላስ ሆቴል አካባቢ ተተክሎ ሳይ ደስ አለኝ፡፡ የተስተካከለውን ማስታወቂያ ማየት ከፈለጉ ይህንን ይጫኑ

    https://plus.google.com/107824562470728028100/posts/VMYUKQA1LsJ

    ReplyDelete