Wednesday, July 25, 2012

አጫጭር ትንፋሾች ፩



በተዘበራረቁ ዕውነታዎች፣ በኑሮ ዳገት እና ቁልቁለት፣ በነፍስ አልባ ንጋት እና ጭለማ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ በዚህች አለም ጫጫታ መሀል ድንገት የሚያነቃው ቢኖር የብቸኝነት የጣት ዕሩምታ ብቻ ነው፡፡ ስነ ኑሮ ብቸኝነትን የቂም ጎጆ፣ የበቀልም መንደርደሪያ ይለው ይሆናል እሱ ግን ከዚህ የተለየ ምናልባት የተሸለ ትርጉም ለብቸኝነቱ ይሰጣል፡፡ በብቸኝነቱ ለጊዜውም ቢሆን ከስጋዊ ጭንቀቱ ርቆ በህሊናው ጫካ ይመንናል፡፡ እንጦጦ አናት ላይ ቤቱን እንዳቆመ ጎበዝ በጊዜ አናት ላይ ሆኖ አላፊ አግዳሚውን ይታዘባል፡፡ ውስጡ ዝም ይልና በቅፅበት፣ በአንዳፍታ ብልጭታ መጪ ህይወቱን ይገምታል፣ ያለፈውን ይገመግማል፡፡ ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ እያጣ በሔደ ቁጥር ምኞቶቹም ከጊዜ  ባላነሰ ፍጥነት ሲነጉዱ ያያቸዋል፡፡ የእርሱ አለም ደግሞ ከምኞት ይጀምራል፡፡ ጥሬ ምኞቶቹን ያለገደብ ከመንገድ ዳርም ቢሆን ያጭዳቸዋል እቅዶቹን ወደ ህይወት ለመዘርዘር ግን ጥሬ ምኞቶቹን ዳግም በብቸኝነት ውስጥ ማመንዠክ ይኖርበታል፡፡ "አሊያማ ሳሩን ብቻ እንዳየው በሬ ወይንም ካፍንጫው ጫፍ ርቀት በላይ ማየት እና ማስተዋል እንደተሳነው ጎረምሳ መሆኔ ነው" እያለም ይጨነቃል፡፡ እናም ፍቀዱለት በብቸኝነት አለም ይናውዝ ዘንድ አትከልክሉት፡፡

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ ኮንጐ )

No comments:

Post a Comment