Monday, August 20, 2012

እኛ እጅ እናወጣለን - እግዚዓብሔር ይመርጣል



ይህችን የጥንት ቤ/ክ ባሰብኩ ቁጥር ልቤን አንዳች ነገር ወደታች ይጫነኛል፡፡ የሀዘን ስሜት ይከበኛል፡፡ የመንግስተ ሰማይ ተምሳሌት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በችግር ተይዛ ስታጣጥር መመልከት እጅግ ያሳምማል፡፡ ለብዙዎች የመፍትሔ ምንጭ የሆነች ቤ/ክ ራሷ ተቸግራ፣ ብዙዎችን ያከመች ቤ/ከ ራሷ ታምማ፣ ታላላቅ ሰዎችን ያፈራች ቤ/ክ ለራሷ የሚሆን ወሳኝ ሰው አጥታ ማየት የእውነትም ይጎዳል፡፡

አባታችን አቡነ ጳውሎስን በሞት ከተነጠቅን ቀናትን መቁጠር ጀምረናል፡፡ እጅግ ፈታኝ ከሆነው እና እንደ እሳት ከሚፋጀው የፕትርክና መንበር ላይ ከተቀመጡ ቀን አንስቶ ተቃውሞ ያልተለያቸው አቡነ ጳውሎስ ላለፉት 20 ዓመታት ቤ/ክርስቲያኗን ሲያስተዳድሩ ቆይተው ወደ ፈጣሪያቸው ሔደዋል፡፡ በእርሳቸው ዘመን ቤ/ክን ብዙ የመከራ አመታትን ብታሳልፍም አባታችን ናቸው እና ሀዘኑ ቤ/ክን ይጎዳታል፡፡ ሀዘኑ እንዳይፀናባት ግን ከችግር የሚያወጣ አፅናኝ አዲስ አባት ያስፈልጋታል፡፡


በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች እንደየሰው አይነት የተለያየ መስሎ ይታያል፡፡ ለታሪክ በሚያሳፍር መልኩ በሁለት ጳጳስ እና በሁለት ሲኖዶስ ስትመራ የከረመችው ይህች ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን መፍትሔ የሚሰጣት አላገኘችም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት እጁን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ባለማንሳቱ እንደ ሙስሊም ወንድሞቻችን ሁሉ እኛም ቤት እሳት አለ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷን ከማዳከም ጀምሮ በግል ጉዳዮቿ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ሲጫወት የነበረውን ሚና በአብዛኛው ምዕመናን በኩል ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ሌላው ራስ ምታት ደግሞ የለሰለሰ የበግ ለምድ ለብሰው፣ የወፍ ድምፅ ይዘው በጉያዋ ውስጥ ተሰግስገው ቤ/ክርስቲያኗን ቀስ በቀስ ለጠላት ሊሰጡ የተዘጋጁት የሌላ ዕምነት አራማጅ ተኩላዎች ጉዳይ ነው፡፡ ለኔ እንደ አንድ ተራ ምዕመን የችግሮቹን ጥልቀት እና አደገኝነት ለመለካት ባይቻለኝም ከሁሉ በላይ እያስፈራኝ ያለው ግን የብፁዕ አባቶች ዝምታ ነው፡፡ አምናለሁ በዝምታቸው ውስጥ ቁጭት፣ ትዕግስት፣ ዕንባ፣ ፀሎት እና ሱባዔ አለ፡፡ ውጊያው ከባድ በመሆኑ ጥንካሬን ይፈልጋል፡፡ አለዚያ ግን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ከመቃብር ልናስነሳ፣ ከሰላም ዕረፍታቸው ልንቀሰቅስ ግድ ይለናል፡፡ ምክንያቱም አባት ያስፈልገናልና፡፡ ለነፍስ ልጆቹ የሚሰዋ፣ ለዓለማዊ ድሎት ያልተሸነፈ፣ ለዕውነት የቆመ አባት ያስፈልገናል፡፡


የአቡነ ጳውሎስን ህልፈተ ህይወት አንዳንዶች እንደ መልካም አጋጣሚ አይተውታል፡፡ ሀሳባቸውን አልቃወምም ለእኔ ግን የሳቸው ሞት ቤ/ክንን መስቀለኛ መንገድ ላይ ያስቀመጠ ከባድ ፈተና ይመስለኛል፡፡ እኛ ወደድንም ጠላን ፓትርያርክን የሚሾመው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር አባት  ሚሾምልን እንድንማር፣ እንድንቀደስ፣ እንቀጣ፣ እንድንማረር፣ ወደ ፈጣሪ እንድንመለስ ሊሆን ይችላል፤ ሹመት ግን የእግዚአብሔር ነው፡፡ እረኛውን ዳዊት ለዙፋን ያበቃው እግዚአብሔር ማንንም ሳያማክር ብቻውን ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህን ክፍተት ለራሳቸው አላማ ለመጠቀም የሚሽሎኮሎኩ አይጦች በሲኖዶሱ ቢሮ ኮሪደሮች ላይ ውር ውር ማለታቸው አይቀርም፣ ሆዳሞችም ምግባቸውን መቃረማቸው አይቀርም፣ ባለስልጣኖችም ሃይላቸውን ለመጠቀም መሞከራቸው አይቀርም፡፡ ግን አንፈራም፡፡ ፍርሃት የክርስቲያን ስላልሆነ አንፈራም፡፡ ይልቅ እንፀልያለን፣ ይልቅ እንፆማለን፣ ይልቅ እግዚአብሔር የጉልበተኞችን ጉልበት ውሃ አድርጎ የባለስልጣኖችን ስልጣን አፈር አድርጎ የመሰሪዎችን ወጥመድ በጣጥሶ፣ ለልጆቹ እውነተኛ አባት እንዲሰጠን በለቅሶና ዋይታ እንለምናለን፡፡ ይሔ ነው የክርስቲያን ደምቡ፡፡


የተለያዩ ወገኖች በተለያየ ጊዜ  ተ ክርስቲያ ሲወ   ኖረዋል ነገር ግን ሁሉም ድል ሆነዋል፡፡ በብፁዕ አባቶች ቡራኬ፣ በካህናት ልመና፣ በምዕመናን ልቅሶና ጩኸት ዲያቢሎስ ድል ያልተመታበት ጊዜ የለም፡፡ ስለዚህም እንደእኔ ፍላጎት ቢሆን ይህ የ16ቱ ቀን ፆም ለተጨማሪ አምስት እና አስር ቀናት በአባቶች ትዕዛዝ ቀጥሎ ምዕመናን በየአድባራቱ ብንለምንበት፣ ብንፀልይበት፣ በዚህ የተቀደሰ የፆም ወቅት ያናገረን አምላክ ሀጥያታችንን ይቅር ብሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነ መሪ እንደሚሰጠን አምናለሁ፡፡

እኛ እጅ እናወጣለን - እግዚዓብሔር ይመርጣል



(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ. ኮንጎ)

No comments:

Post a Comment