Saturday, August 11, 2012

ኮንጎሊዝ - የጉዞ ማስታወሻ


የፓትሪስ ሉሙምባ ሃገር  ዲ.ሪ.ኮንጎ ዋና ከተማ የሆነችው ኪንሻሳ እብድ ያደረበት ቤት እንደመሰለች ይኸው ዛሬም ከንጋት ተገናኝታለች፡፡ ካለፈው ሳትማር፣ ከትላንት ሳትለወጥ ትላንት እንዳየናት ይኸው ዛሬም ከነአደረ ፊቷ ፀሀይ ትሞቃለች፡፡ አንዳንዴ ቤቴ ከቢሮዬ ብዙም ባለመራቁ ደስ ይለኛል፡ ምክንያቱም የዳይመንድ ሃብታቸው እየተዛቀ ወደ ምዕራባውያን የሚጋዝባቸውና የበይ ተመልካች ሆነው ከድህነት ጋር በፍቅር የወደቁ ሰዎችን ለረዥም ሰዐት ማየት ያሳምማልና፡፡ የመኪናውን ግርግር አልፌ ራመድ ራመድ እያልኩ ቢሮዬ ገባሁ፡፡

ፊቴ ላይ ያለውን ፀጉር ከመጠኑ በላይ እጅብ ማለቱ ሲያስጨንቀኝ ስለዋለ መስተካከል ፈልጌ የስራ ባልደረባዬ የሆነውን የሀገሩ ተወላጅ ሪዲን በአካባቢው ያለ ፀጉር ቤት እንዲወስደኝ ሳማክረው በተለመደ የታዛዥነት ስሜት ማታ ከስራ ስንወጣ እንደሚወስደኝ ነገረኝ፡፡ ይህ የስራ ጓዴ ከፈረንሳይኛና ሊንጋላ ውጪ በመጠኑም ቢሆን እንግሊዝኛ አፍ ስላለው እንዲህ አይነት ቦታ ላይ እሱን ማማከር ይስማማኛል፡፡ ሪዲ ህልሙ ሁሉ አሜሪካ ናት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለመሔድ ሞክሮ ቪዛ ከልከሉንና አሁንም ግን ተስፋ እንዳልቆረጠ አጫውቶኛል፡፡ ስለኢትዮጵያ ወሬ ሲነሳ ሁልጊዜ የሃይሌ /ስላሴን ስም ይጠራልኛል፡፡

ሙሉ ቀን ኮምፒውተሬ ላይ ተደፍቼ ስለምውል ቀኑ ከመቼው ነጉዶ እንዲህ ድንግዝግዝ እንደሚል ባላውቅም ሂሳቤን እና ኮምፒውተሬን በፍጥነት ዘጋግቼ ሪዲን ተከትዬ ወጣሁ፡፡ ለአይን ያዝ ባደረገው ምሽት የሰው ብዛት ረገብ ብሏል፡፡ ግራ ቀኙን እያማተርን ትንሽ ሄድ እንዳልን ሪዲ ቆም አለና "ዘግተዋል መሰለኝ" አለ ወደ አንድ አቀወጣጫ እየተመለከተ፡፡ ትንሽ ግራ ገባኝ እሱ ወደሚመለከትበት አቅጣጫ ብመለከት ከአንድ መጠጥ ቤት ውጪ የተከፈተም ሆነ የተዘጋ ንግድ ቤት አይታየኝም፡፡ ሪዲ ወዲያው ሀሳቡን ቀይሮ "አይ አይ ክፍት ነው" አለና በፍጥነት ወደ መጠጥ ቤቱ ተራመደ፡፡ እንግዲህ ወይ ፀጉሬን የሚቆርጠኝ ሰው እዚህ መጠጥ ቤት ውስጥ እየተዝናና ነው አሊያም ፀጉር ቤቱን ለማግኘት በመጠጥ ቤት ውስጥ አቋርጠን ማለፍ ይኖርብን ይሆናል ብዬ ተከተልኩት፡፡ በረንዳው ላይ ስድስት የሚሆኑ ሰዎች የሃገራቸውን ተወዳጅ ቢራ /SKOL/ ይዘው ይጨዋወታሉ፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ እጅብ እጅብ ብለው እየተሳሳቁ ሚጠጡ ሌላ ባልኮኒ ላይ ተሰቅለው የኮፊ ኦሎሚዴ ሙዚቃ እንደ ትኩስ ትንፋሽ የሚፈጃቸው የሚመስሉ የተከዙ ሰዎች አሉ፡፡ የሴቶቹና መብራቱ ሁኔታ ቤቱን ከአዲስ አበባ ቺቺኒያ ከሚባለው ሰፈር ተነቅሎ የመጣ አስመስሎታል፡፡ እዚህ መጠጥ ቤት ውስጥ ምን ልናደርግ እንደመጣን ባይገባኝም ሪዲ እና የቤቱ ኃላፊ ወደ እኔ እየጠቆሙ ይነጋገራሉ፡፡ ኮንጎሊዞች አንድን ነገር ለማስረዳት ትንፋሻቸው እልቆ ምራቃቸው እስኪደርቅ ማውራት ስለሚወዱ ነገሩ በቀላሉ እንደማያልቅ ገብቶኝ ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ፡፡ ዙርያውን ያለው የቤቱ መስታወት ቀዩን ብርሀን እያንፀባረቀ ይመልሳል፡፡ ሪዲ ወደ እኔ ተመልሶ "በቃ አዚሁ ያለህበት ይቆርጥሀል" አለኝ፡፡ የሰማሁትን ተጠራጥሬ "አልገባኝም?" አልኩት፡፡ ቀለል አድርጎ "ይኸው እሱ ነው የሚቆርጥህ" ብሎ ወደ አንደኛው አስተናጋጅ ጠቆመኝ፡፡ "የት እዚህ? መጠጥ ቤት ውስጥ? ይሔ ሁሉ ሰው እያለ?" ጥያቄዬን አላቆምኩም "ደግሞስ በምን ብርሃን ሊቆርጠኝ ነው?" ሪዲ ምንም ሳይደናገር ፈገግ አለና "ችግር የለውም አንተ እኮ አሁን ኮንጎሊዝ(ኮንጎአዊ) ሆነሃል እንደ እኛ ነው መኖር ያለብህ፡፡ ይሔ ቤት መጠጥ ቤት ነው ነገር ግን ፀጉሩን መስተካከል የሚፈልግ ሰው ሲመጣ ደግሞ ፀጉር ቤት ነው፡፡ አይዞህ አትፍራ አንተ እስክትጨርስ ድረስ ዋናው መብራ ይበራልሃል ሰዎቹ ምንም አይሉም ይሔ የተለመደ ነው" አለኝ፡፡ መብራቱ፣ ሙዚቃው እና የሪዲ ንግግር ተደበላለቀብኝ፡፡

በርግጥ እኔ ከስካንዲኒቪያን ሃገሮች አሊያም ሆንግኮንግ ወይንም ካናዳ አልመጣሁም፡፡ እጅግ ዘመናዊና ፍፁም ንፁህ ነገርንም አልጠበቅኩም ግን ቢያንስ አዲስ አበባዊ እንደመሆኔ ፀጉር እና ወደ ሆድ የሚገቡ ነገሮች ለየቅል የሚቀመጡ መሆናቸው አይጠፋኝም፡፡ ፈዝዥ እንደተቀመጥኩ መብራቱ ቦግ ብሎ በራ፣  ተስተናጋጆቹ ወደእኔ ዞር ብለው አይተው ወደ ጨዋታቸው ተመለሱ፣ አፈርኩ፡፡  አስተያየታቸው እኔን "አላዋቂ ነህ፣ ከየት አገር የመጣህ ባላገር ነህ" የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ፀጉር አስተካካዩ (A.K.A. አስተናጋጁ) አንድ ማበጠርያ እና ቶንዶስ ይዞ ፍቃዴን ሳይጠይቅ ያበጥረኝ ገባ፡፡ አሁን ምርጫ እንደሌለኝ ሳውቅ ሳቅ አፌን ሞላው፡፡ ተደበላልቆ የነበረው ስሜቴም ቀስ እያለ መስመር መያዝ ሲጀምር የሀገሬን ዘፈን ጮሔ መዝፈን ዳዳኝ . . .

ወይ አዲስ አበባ

ወይ አራዳ ሆይ . . .

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ. ኮንጎ)

3 comments:

  1. Ahahaa wendimen wendimen . . . Alexi I am so glad that you are testing this extreme of life coz i strongly beleve that it will help u some time even when u'll be in addis. Ayzo be strong alexi.

    ReplyDelete
  2. such is life Alex! I am sure you are enjoying all the differences and crazy experience. Thank you for sharing

    ReplyDelete
  3. ze yigerm neger naw! አድቬንቸሩ ደስ ይላል፤ የጤና ሪስኩ ግን ‹አውጣኝ!› ያሰኛል፡፡ ያውጣህ፡፡

    ReplyDelete