Thursday, August 23, 2012

ኮንጎ - የጉዞ ማስታወሻ ፪


ከሰሞኑ አንድ ምሽት ላይ ከኪንሻሳ ወጣቶች ጋር የባጥ የቆጡን ሳወጋ ነበር፡፡ እንደአብዛኛው የሀገሪቱ ወጣቶች ሁሉ የአለም መጨረሻው ፈረንሳይ ድምበር ከሚመስላቸው ከእነዚህ ጓደኞቼ አንዱ ታድያ ድንገት በጨዋታው መሃል ስለ ኢትዮጵያ ሲያነሳ ቀልቤን ሰበስቤ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ሲጓዝ በአዲስ አበባ በኩል ትራንዚት አድርጎ እንደነበር እና የአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ በአግራሞት ተናገረ፡፡ እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያ እንዴት እያደገች እንዳለች ለተቀሩት ማስረዳት ቀጠልኩ፡፡

በመሀል ግን አንድ በጥሞና ሲያዳምጠን የነበረ ሰው "ይቅርታ አድርግልኝና አሁን ስለኢትዮጵያ የምታወሩትን ነገር በአእምሮዮ ለመሳል በፍፁም አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም እኔ ትምህርት ቤት እያለሁ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሰቃቂ ረሃብ ላይ ስለሆነ እርዱ እየተባልን በየክፍላችን ከረጢት ይዞር ነበር" አለኝ፡፡ ረዥም አመታት በአውሮፓና አሜሪካ ቆይተው የመጡ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ነገር በየቀኑ እንደሚሰሙት አውቃለሁ እኔን አሁን የገረመኝ ግን ይሔንን የሚለኝ ሰው የኮንጎ ሰው መሆኑ ነበር፡፡ ምናልባት ኮንጎን ለማያውቃት ኢትዮጵያዊ ይሔ ንግግር ላይደንቀው ይችላል፡፡ ኮንጎ ማለት ግን ህዝቦቿ ከድህነት ጋር በፍቅር የወደቁባት፣ ዝርፊያ፣ ቅሚያ እና ሙስና ያለቅጥ የሰፈነባት (ኮንጎን ያላየ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና አለ ይላል)፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተብሎ ከመጠራት ውጪ ዲሞክራሲ የሚለው ቃል ጭራሽ የሌለባት፣ ዋና ከተማዋ ውስጥ በቀን ቢበዛ ከአራት ሰዓት በላይ መብራት የማይገኝባት፣ የሀገሪቷን ገንዘብ ጥለው በዶላር የሚገበያዩባት፣ ፖሊስ በቀን ብርሃን ሰው አስቁሞ የሚዘርፍባት፣ በአጠቃላይ ህግና ፍትህ  የሌለባት ሀገር ናት፡፡

እውነቱ ይሔ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ከኮንጎ የባሰች የጨለመች ሀገር መስላ እንድትታይ ያደረገው ሃቅ ወይንም በድሆቹ ኮንጎሊዞች ውስጥ እንኳ ሳይቀር እንዲህ አይነት ሀሳብ የሰረፀበት ምክንያት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ባለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ዘመቻ ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ተርበን እንደምናውቅ አልክድም፣ በየሰው ደጃፍ ከረጢት እንደዞረልንም አውቃለሁ ነገር ግን እጅግ በጣም ብዙ መልካም ነገሮችም አሉን፡፡ እንኳን ኮንጎ፣ ስልጥን ያሉት ሀገራት የሌላቸውን ጀግንነት፣ ታሪክ፣ ሞራል፣ ስነምግባር እና ጥሬ ዕቃ አለን፡፡ እኒህን ለአለም አሳውቀን ለስማችን ማስተካከያ ካልነገድንባቸው ግን ሁሉም ባዶ ናቸው፡፡ የአክሱምን ጥበብ፣ የአለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ዝና፣ የወንዞቻችንን አቅም የህዝባችንን መተሳሰብ አለም እስኪሰለቸው ካልነገርነው እና ስማችንን ካላደስንበት ሁሉም ትርጉም የለሽ ነው፡፡

የ21ኛው ክ/ዘ ትልቁ መሳርያ (ሚዲያ) ነው፣ ለኢትዮጵያ አራት አመት ጠብቆ ብቅ የሚለው ኦሎምፒክ ብቻውን ገፅታዋን ሊያስተካክል አይችልም፡፡ ጠላቶቻችን ስማችንን እንደቋንጣ እያደረቁ አለም በረሃብ እንዲስለን በየመገናኛ ብዙሃኑ ከዘመን ዘመን እንደታገሉ ሁሉ እኛም ደግሞ ስማችንን ለማደስ እነሱ የሔዱበትን መንገድ መሔድ ይኖርብናል፡፡ አለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሐን ስለእኛ ደግ ደጉን የሚያወሩበትን መንገድ መፈለግ ይኖርብናል፡፡  . . . አሁን ግን ለዚህ ኮንጎሊዝ ምላሽ መስጠት አለብኝና ወደ እርሱ ልመለስ፡፡
 

(ዲ.ሪ.ኮንጎ - ኪንሻሳ)

No comments:

Post a Comment