Sunday, February 8, 2015

ሔዋኔ


እንዲሁ እንደነቃሁ በአይኖቼ መገለጥ መሀል በቅዠት የተዋዛ፣ በራዕይ የተለወሰ ህልም አያለሁ፡፡ የሚጣፍጥ ህልም፣ በፀጋ የሚያላብስ ህልም፡፡ እንዲሁ እንደነቃሁ . . . እርሷን አያታለሁ፡፡


አንዳንዴ እንደ ርግብ አንዳንዴ ደግሞ እንደ መልከመልካም ሴት ትመሰልብኛለች፡፡
አላውቃትም እርሷም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ሩቅ ባለ ሀገር ሆና እንደ አፍንጫዬ ጫፍ ትቀርበኛለች፡፡ በሰው ይሁን በመላዕክት፤ በርግብ ይሁን በእፉዬ ገላ ቋንቋ፣ ብቻ በለሆሳስ ታናግረኛለች፡፡ በጥቅሻ ትጠራኝና ስጠጋት በድኔን ትታ ነፍሴን አፈፍ አድርጋ ነጫጭ ክንፎቿን እያማታች ወደ ከፍታ ላይ ትወስደኛለች፡፡ የከፍታው  ርዝመት ዛሬን አሳልፎ ነገን ያሳያል፡፡ በርቀት እንደ ፀሀይ መውጣት እየወገገ ወደሚታየው ነገ ላይ የክንፏን ጫፍ እንደጣት ቀስራ በውብ ሴት ድምፅ እንዲህ ትለኛለች “ያ ከዛሬ ድንበር ማዶ ያለው ነገ ይታይሃል?” “አዎን ይታየኛል” እላታለሁ አይኖቼን ከአይኗ ሳልነቅል፡፡ “ነገዬን፣ ተስፋዬን፣ ስኬቴን ላካፍልህ እሻለሁ፡፡ የነገውንም ነገ እንዲሁ እስከዘለዓለሙ፡፡ እባክህ አብረኸኝ ሁን . . .” እሺታዬን አገጬን ወደ ግንባሬ፣ ግንባሬን ወደ አገጬ በመወርወር እገልፅላታለሁ፡፡ ይህች የኖህ ርግብ፣ ይህች መልካም ጉብል ከየት ተከሰተች? ይህቺስ ከጉንጭ የተነሳ ንፋስ የማትችል እፉዬ ገላ ከየት ስትበር መጣች? . . . መልስ የለም ግን እጠይቃለሁ እመራመራለሁ፡፡

እንዲሁ እንደነቃሁ በአለም ጫጫታ መሀል በፀጥታ የተሞላ፣ በዝምታ የሰከነ ህልም አያለሁ፡፡ የሚያፈዝ ህልም፣ ሳቅን በአፍ የሚሞላ ህልም፡፡ እንዲሁ እንደነቃሁ . . . እርሷን አያታለሁ፡፡
አንዳንዴ እንደ ርግብ በርራ ታበርረኛለች፣ አንዳንዴ ደግሞ እንደ መልካም ሴት ገላዬን በውድ ዘይት ታሸኛለች፡፡ ጆሮዎቼንም በመልካም ወሬ ታረሰርሳቸዋለች፡፡ በሰውኛ ይሁን በመላዕክትኛ፤ በርግብኛ ይሁን በእፉዬ ገላኛ ቋንቋ፣ ብቻ በሹክሹክታ ታናግረኛለች፡፡ ድምፅዋ የተስፋን ወኔ ይቀሰቅሳል፣ የፍቅርን ህዋስ ያነሳሳል፡፡ “አንተ እኮ . . .” ትለኛለች በምስጠቴ መሀል “. . . አንተ እኮ እንደመልካም ቅላፄ እንደሚለሰልስም ሙዚቃ ትመስጣለህ፣ እንደ ምስጋና ትጣፍጣለህ፣ እንደ የሚያምር ህፃንም ታሳሳለህ” ትለኛለች፡፡ በዚህ ግዜ እንኳን እኔ ምድር ራሷ ፈዝዛ ስበቷን ረስታ ትለቀኛለች፡፡ ሳላውቀው እንሳፈፋለሁ፡፡ ድንገት አፈፍ ታደርገኝና ቁልቁል እያየችኝ አድነኝ በሚል ገፅታ በማሳዘን ትመለከተኛለች፡፡ ምስጢሯን ገልፃ የትላንት ቁስሏን እያሳየችኝ ፈውሰኝ ትለኛለች፡፡ ይህችን የመሰለች ርግብ ማን በቀስት ጫራት? ይህችን መልካም ሴት ማን ወንድ ተዳፈራት? ይህቺስ እፉዬ ገላ ምን ጋሬጣ ስስ ገላዋን አረገፋት? . . . መልስ የለም ግን እጠይቃለሁ እመራመራለሁ፡፡

እንዲሁ እንደነቃሁ በጉስቁልናዬ መሀል በተስፋ የተሞላ፣ በዓላማ የጠነከረ ህልም አያለሁ፡፡ ማመን የሚያቅት ህልም፣ ተረት የሚመስል ህልም፡፡ እንዲሁ እንደነቃሁ . . . እርሷን አያታለሁ፡፡
አንዳንዴ እንደ ርግብ ከአፏ በአፌ ትመግበኛለች አንዳንዴ ደግሞ እንደመልካም ሴት ለእግሬ ውሃ አሙቃ ትጠብቀኛለች፡፡ ድካሜ ሲደክማት፣ ደስታዬ ሲያለመልማት ይሰማኛል፡፡ እልፍ ሰው መሀል ሆና በፀጥታና በብቸኝነት እጆቿን ዘርግታ እየተሸከረከረች የምትደንስ እፉዬ ገላ ሆና ትታየኛለች፡፡ እንዳልይዛት ርቃኛለች እንዳልረሳት ረግሞ በዓይኔ ብሌኖች ላይ ተስላለች፡፡ በሩቅ ሀገር ያበቀልኳት መንደሪን፣ በሰማይ ያለችኝ ላሜ ናት፡፡ ርቀታችን ሲሻው ከዚህ እስከጨረቃን  ይልቃል ሲለው ደግሞ ሰይፍ የማያሳልፍ ይሆናል፡፡ አላስችልህ ሲለኝ ዝምታዬን ሰብሬ ከናፍሮቼን አላቅቃለሁ፡፡ ገፅዋ ላይ የሌለ፣ ነገር ግን በአእምሮዬ ውስጥ የተሳለ ውበቷን በእፉዬ ገላኛ እነግራታለሁ፡፡ ከዚያም በተራዬ አይኖቼን ጨፍኜ እሰማታለሁ፡፡ ያለኝ ውድ ንብረት ድምጿ ነውና እሰማታለሁ፡፡ አንዳንዴ እንደ ርግብ አንዳንዴ እንደ መልከመልካም ሴት ሌላ ግዜ እንደ እፉዬ ገላ ትመሰልብኛለች፡፡ ግን ምንድነች? ርግብ ትሆን? በርራ የምታበርረኝ? በማያልቅ መልካም ብስራት ነፍሴን የምትሞላኝ? ወይንስ መልከመልካም ሴት ትሆን? በጎደለ ሙዪ ተብላ የተላከች? ምናልባትስ እፉዬ ገላ ከሆነች? ቁንጅናዋ የሚማርክ ሲይዟት ደግሞ በጣት መሃል እየሾለከች የምታጫውት? . . . መልስ የለም ግን እጠይቃለሁ እመራመራለሁ፡፡

አለማየሁ አ. ኪዳኔ

ጥር 2007ዓ.ም

No comments:

Post a Comment