Saturday, April 27, 2013

አንዳንድ ብሽቅ ሰዎች




ቅዳሴ መሃል ነው፡፡ “በንሰሃ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” በሚለው የካህን ትዕዛዝ መሰረት በመቅደሱ ውስጽ ካሉት ጀምሮ ከደጀ ሰላሙ ቅጽር ውጪ እስካሉት ሰዎች ድረስ ግማሹ ከወገቡ ጎንበስ ከጉልበቱ ሸብረክ ብሎ የሁለት እጆቹን መዳፍ ለፈጣሪው እያሳየ ግማሹ ደግሞ በግንባሩ ተደፍቶ በፍፁም ፀጥታ ተውጠዋል፡፡ በድምፅ ማጉያው ከሚሰማው ከካህኑ የእግዚዮታ ድምፅ ውጭ ምንም ነገር አይሰማም አይንቀሳቀስም፡፡
የቤተክርስቲያን ውበት የሆኑት ዛፎች እንኳን ወፎቻቸውን ገስፀው ያለምንም እንቅስቃሴ በተመስጦ ቆመዋል፡፡ አስቡት እንግዲህ ድባቡን! ታዲያ በዚያ በሚያስፈራ ፀጥታ መሃል ድንገት አንድ ሰው “ሃሎ ስንሻው” ብሎ ከሔዳችሁበት ሰባተኛው ሰማይ መንጥቆ ሲመልሳችሁ አያናድድም? ቀና ብላችሁ ስታዩት የሆነ ቦርጩን በለበሰው ቱታ ውስጥ መደበቅ ያልቻለ ሰውዬ በንሰሃ ውስጥ ባሉት ሰዎች መሃል ዘና ብሎ እየሄደ ሰውን ሁሉ ከሰባተኛው ሰማይ ወደ ምድር እያፈረጠው መሆኑን ስታዩ የሆነ መኖሩን እንኳ የማታውቁትን ደም ስራችሁን ከቆዳችሁ በላይ ይወጣል፡፡ ደግሞ እኮ ስልክ እያወራ በሰው መሃል መሔዱ ብቻ እኮ አይደለም የሚያበግነው ይባስ ብሎ አንድ እጇን ይዞ ለሚጎትታት ህፃን ልጁ ያደረገላት ጫማ ስትረግጠው “ፂጥ . . ፂጥ . . . ፂጥ. . . በቃ ምን ልበላችሁ!? ግማሹ በቀላሉ የማይገኘውን የሰባተኛውን ሰማይ ሊፍት እያማተበ ይጣራል ግማሹ ማጉረምረም ይጀምራል፡፡ ቦርጫሙስ ሰውዬ? ይደንቀዋል እንዴ? እኔማ እንደው ያን ነገሬን ነው የሚያመጣብኝ፡፡ ኸረ በናታችሁ!!! እንዴት ሰው ለልጁ እንደዛ አይነት ድምፅ የሚያወጣ ጫማ አድርጎ ቤተክርስቲያን ያውም በቅዳሴ ሰዓት ይዞ ይሔዳል?? ደግሞስ ሰው ሁሉ አጎንብሶ ሲያይ እንደው ፀሎቱስ ይቅር ምን ወድቆ ነው ተብሎ እንኳን ጎንበስ አይባልም? ብሽቅ ነገር፡፡የምር ግን ለአካባቢው የማይጨነቅ ሰው አያበሳጫችሁም? እኔ የሆነ ምግብ የሚበላበት ቦታ ላይ ሲጋራ የሚያጨሱ አይነት ሰዎች ሳይ ፀብ ፀብ ነው የሚለኝ፡፡ የነሱን ማጨስ እንጂ የሌላው መመገብ ምንም አይመስላቸውም፡፡እሱስ ይሁን አለላችሁ እንጂ ይሔኛው ጉድ፡፡ የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብላችሁ ተቆራጭ ነገር እየጎረሳችሁ አንድ መንገደኛ በስነስርዓት ሲራመድ ቆይቶ ልክ እናንተ ያላችሁበት ጋር ሲደርስ ቆም ብሎ በሚያስደነግጥ መልኩ ከጉሮሮው ይሁን ከአንጎሉ ብቻ የሆነ ነገር እያኩረፈረፈ ማግ ያደርግላችኋል፡፡ እናንተ አፍ ውስጥ ያለውን ተቆራጭ እና እሱ አፍ ውስጥ ያለውን ጉድ አስቡት እንግዲህ፡፡ እናንተ የራሳችሁ አፍ አስጠልቷችሁ ከአሁን አሁን ይተፋዋል ብላችሁ ስትጠብቁት አጅሬ ጭራሽ ዋጥ ያደርጋትና እርፍ ይልላችኋል፡፡ ይሔ ነው የጀግና ወጉ እንግዲህ፡፡ በቃ ምን ታመጣላችሁ? ለምን ዋጥከው አትሉት የራሱ ነው፡፡ እኔ እኮ የሚገርመኝ የአንጎል ፅዳት ነው እንዳልል በየመንገዱና በየታክሲ ውስጥ እንዲህ አድርጎ መፀዳደት ነውር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሲቀጥል ይህ ድርጊት ሌላ ሰውን ስለሚያስፀይፍ ቢቻል ሰው በሌለበት ራቅ ባለ ቦታ ለምን እንደማይደረግ አይገባኝም፡፡ ኤጭ ብሽቅ ብቻ ነው የሞላው ልበል?

አዲስ አበባ

1 comment: