Friday, April 26, 2013

ኢትዮጵያ ማለት እኔ ነኝ - ይድረስ ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች



ይድረስ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላልተደሰታችሁ እና ኢትዮጵያን እናንተ መልካም ነው ወዳላችሁት ጎዳና ለመውሰድ ለምትጥሩ የተቃዋሚም ሆነ የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች፡፡

ይህ መልዕክት ያሰባችሁትን ሁሉ ለማሳካት ሊፈቅድላችሁም ሆነ ሊከለክላችሁ ከሚችለው ከመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መሀል የአንዱ ድምፅ ነው፡፡
ድምፅ ማለቴ በእውነተኛ ዲሞክራሲ ውስጥ ያሻውን ሊመርጥ የሚበጀውን ሊናገር የሀገሪቱን እጣ ፈንታ ሊወስን እንዲችል ባለሙሉ ስልጣን የሆነውን የህዝብ ድምፅ ማለቴ ነው፡፡ ይህ ድመፅ በእርግጥ በኢትዮጵያችን እንደተለመደው በግድ የፊጥኝ ታስሮ በጥቅም ተታሎ ራስን በመውደድ አሊያም በሌላ ሌላ ምክንያት መብቱን ለሽያጭ ያስቀመጠ ድምፅ አይደለም፡፡


እናም ሊሰማኝ የሚችል ጆሮ ካላችሁ ልሰጣችሁ የምችል ድምፅ አለኝ፡፡ ጫካ ብትገቡ፣ አዲስ አይነት የፖለቲካ አብዬት ብታራምዱ፤ የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ብትሆኑ፣ አኩራፊና ተገንጣይ ፖለቲከኛ ብትሆኑ ከላይም ብትመጡ ከታችም ብትሆኑ ያሰባችሁበት ሊያደርሳችሁ የሚችለው ብቸኛው ስንቃችሁ የእኔ ድምፅ አለላችሁ እናንተ ጆሮ ካላችሁ፤፡ የሀገሬን ታሪክ እንድትቀይሩ፣ የልጆቼን ተስፋ እንድታለመልሙ የሚያስችላችሁ አንድ ድምፅ አለኝ ልትጠቀሙበት ከቻላችሁ፤፡

በየአምስት አመቱ ድምፄን ለማግኘት ስትሯሯጡ አያለሁ ነገር ግን ድምፄን ለማግኘት ልቦናዬን፣ ልቦናዬን ደግሞ ለማግኘት ጆሮዬን ማሸነፍ እንዳለባችሁ ዘንግታችሁታል፡፡ አሁንም በቃላት ሽንገላ ልትሞሉኝ ትፈልጋላችሁ፣ ያለፈ ቁስሌን በመነካካት ህይወቴ መለወጡን ልታሳምኑኝ ትሻላችሁ፣ ውሃ የማይቋጥር፣ እንደጉም የሚተን እና እርስ በርሱ የሚጋጭ ዕቅድ ልትግቱኝ ትታገላላችሁ፡፡ እንኳንስ ልቦናዬን አሳምናችሁ ድምፄን ልሰጣችሁ ቀርቶ ለጆሮዬ የሚስብ ነገር እንኳን የላችሁም፤፡ በእርግጥ የእኔ ድምፅ አንድ ነው ሃሳቤ ግን የብዙዎች ነው ስለሆነም ድምፄን ለማግኘት መጀመርያ የምፈልገውን እወቁ፡፡

ከሁሉ መጀመርያ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል አስቀድሙ፡፡ የእኔ እና የናንተ ጉዳይ እርሷው ናትና፡፡ ሃሳብ ምኞት እቅዳችን ሁሉ ስለ እርሷው መሆኑን እወቁልኝ፤፡ እንጂ ስስ ገላዬን ያገኛችሁ መስሏችሁ በጎጥ አመለካከት ተወጥራችሁ አትምጡብኝ፡፡ የብሔር ዣንጥላ ይዛችሁ እንድጠለል አትጥሩኝ ምክንያቱም ቤቴም ብሔሬም ሃይማኖቴም ኢትዬጵያዊነት ነውና፡፡ የኦሮሞ ግንባር፣ የአማራው ክንፍ፣ የአፋር ትከሻ፣ የትግሬ መከታው ነን አትበሉኝ፡፡ ይህ ንግግራችሁ ለእኔ ጆሮ የሚቀፍ ነው፡፡ ድምፄን ከኮሮጆው እንዳኖርላችሁ ከፈለጋችሁ ስለኢትዮጵያዊ ሁሉ ታገሉ፣ ስለ ሲዳማውም፣ ስለ ጉራጌውም፣ ስለ ኦሮሞውም፣ ስለ ትግሬውም ይቆርቁራችሁ፡፡ ያን ግዜ ጆሮዬን እሰጣችኋለው ቀጥሎ ስለምትነግሩኝ ነገር ለማዳመጥም እዘጋጃለሁ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሰው በመሆኔ ብቻ አምላክ የሰጠኝ መብቶች ላይ ፈፅሞ እንደማልደራደር እንድታውቁልኝ እወዳለሁ፡፡ የመኖር፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመማር፣ የመስራት፣ መሬት የማግኘት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የመናገር ነፃነቴን እንዲሁም ስለፈለኩት ጉዳይ መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘት መብቴ ህገ-መንግስታዊ እንዲሁም ሰማያዊ ስጦታዬም ጭምር በመሆናቸው በእናንተ መልካም ፍቃድ የምትፈቅዱልኝ እና የምትከለክሉኝ ሳይሆን የእናንተ ግዴታ ይህንን መብቴን ልትጠብቁልኝ ብቻ መሆኑን ቃል ከመግባት ባለፈ ልታሳምኑኝ ግድ ይላችኋል፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የእኔ ድምፅ ለግል ጥቅም ሲባል የሚሸጥ ሸቀጥ ስላልሆነ መምረጥ ካለብኝ ከነነፃነቴ መደህየትን እንጂ በተኮላሸ ማንነት መበልፀግን የነውር ያህል እፀየፋለሁ፡፡ ይህም መብቴ በመሆኑ የግል አመለካከቴ እንዲከበርልኝም እሻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ማለት እኔ ነኝ የእኔን ሰብዓዊ መብት ስታከብሩ ቤቴን ታከብራላችሁ፣ ቤቴን ስታከብሩ የአካባቢዬን መብት ታከብራላችሁ፣ ያ ማለት ስለሁላችንም መብት ትጨነቃላችሁ፤፡ ያን ባደረጋችሁ ግዜ አምናችኋለው ቀጥሎ ስለምትነግሩኝ ነገር ለማዳመጥም እዘጋጃለሁ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ንቀታችሁን አስወግዱ፡፡ ይህ ህዝብ ምን ያውቃል አትበሉ፡፡ ዲሞክራሲ ይበዛብሃል፣ የምትፈልገውን እና የሚያስፈልግህን እኛ ነን የምናውቅልህ አትበሉኝ፡፡ መች ዲሞክራሲ ተሰጥቶኝ አያችሁ እና ዲሞክራሲን ለመሸከም የሚያስችል ጫንቃ እንደሌለኝ አወቃችሁ? መች በነፃነት አወራሁ እና የምፈልገውን በሚገባ ተረዳችሁ? መች አማከራችሁኝ እና ስሜቴ ተሰማችሁ? ይልቁንስ ጠይቁኝ እነግራችኋለው፣ አክብሩኝ እደግፋችኋለው፡፡ ያን ባደረጋችሁ ግዜ አግዛችኋለው  ቀጥሎ ስለምትነግሩኝ ነገር ለማዳመጥም እዘጋጃለሁ፡፡

በመጨረሻ በልባቹ የሚንቀለቀል የበቀል እሳት ካለ አጥፉ እንደጎረምሳ በስሜት አትነዱ፡፡ ከእኔ የወሰዳችሁትን ድምፅ ትላንት በስልጣን ላይ ሳለ ለበደለን መበቀያ እንድታውሉት አልሻም፡፡  ስልጣናችሁን ለስሜታችሁ መወጫ ለግል ፍላጎታችሁ መጠቀሚያ እንድታደርጉትም በፍፁም አልፈቅድም ሌላ ቁርሾ ለመፍጠር ከሆነ አትልፉ፣ ሌላ ጭካኔን ለማስተናግድም ከሆነ ጊዜያችሁን አታባክኑ፡፡ ይልቅ ቅራኔን በብሔራዊ ዕርቅ እንደምታሸንፉት ሳውቅ ያን ግዜ አመርጣችኋለው ቀጥሎ ስለምትነግሩኝ ነገር ለማዳመጥም እዘጋጃለሁ፡፡

ይህን የማደርገው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይህ ብቻ ስለሆነ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ስለማይገባትም አይደለም ይልቁንስ ከምንም ነገር በላይ በእነዚህ ነጥቦች ዙርያ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋናዬች ነን ከሚትሉኝ ሰዎች ጋር ስለማልስማማ እንጂ፡፡ ብደግፋችሁ የሃሳባችን መስመሩ ገጥሞ የዓላማችን ሰንደቅ ኢትዮጵያ ስለሆነች እንጂ የጠላቴ ጠላት ስለሆናችሁ አይደለም፡፡ ባልከተላችሁም ወይ ድብቅ ዓላማ ቢኖራችሁ፣ ወይንም “ዝንጀሮ ቢሔድ ጦጣ ተተካ” ብትሆኑብኝ፣ አሊያም ሙሴን የመሆን ዓቅም ብታጡ እንጂ ባንዳ ሰለሆንኩ አይምሰላችሁ፡፡  ኢትዮጵያ ማለት እኔ ነኝ ገበሬው፣ አስተማሬው፣ ህፃን፣ ሴቱ፣ አማራው፣ ደቡቡ፣ ነጋዴው፣ ተማሪው እኔ ነኝ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መራጩ እኔ ነኝ፡፡ እኔ ግን ድምፄን በከንቱ አላባክንም፡፡ ለጊዜው የተቀደሰው ነገር በዙርያዬ ባይኖርም ለረከሰው አላድርም፡፡ በመብቴ ላይ ተስፋ አልቆርጥም ለግዴታዬም ወደ ኋላ አልልም፡፡ አውሩኝ ስለ ኢትዮጵያ እሰማችኋለው፣ መብቴን ጠብቁልኝ አምናችኋለው፣ አሳትፉኝ አግዛችኋለው፣ ለፍትህ ቁሙ እመርጣችኋለው፡፡

አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment