Thursday, October 4, 2012

የትኛው ድሮ



እድሜያቸው ዘጠና ዓመት የሞላቸውን አዛውንት ስለድሮ ብንጠይቃቸው ያለምንም ጥርጥር ከስልሳ አመት በፊት ስላለው ነገር ያጫውቱናል፡፡ የሀምሳ አመት ሽማግሌንም እንዲሁ ብንጠይቅ ከሀያ አምስት አመት በፊት ስላለው ጉዳይ ነው የሚነግሩን፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ የድሮ ትርጉሙ እንደ አጫዋቹ ይለያያል ማለት ነው፡፡
እኔና “አባቴ” ባለፈው ስንጨዋወት በወሬው መሃል “በጣም ይገርምሃል አይኔ እኮ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ያለምንም ችግር መነፅር እንኳን ሳላደርግ ማየት እችል ነበር” አለኝ፡፡ በጣም ገረመኝ ምክንያቱ ደግሞ አሁን አይኑ ያለበትን ደረጃ ስለማውቅ ቅርብ ጊዜ ድረስ አጥርቼ እመለከት ነበር ሲል ምንቢሆን ነው እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጨናበሰው ብዬ ነው፡፡ እናም “አጭር ጊዜ ስትል መቼ” ብዬ ጠየቅኩት “ኸረ . . . ቅርብ ጊዜ ስልህ አስር ዓመት አካባቢ” ብሎኝ ቁጭ፡፡ መልሱ ክው አደረገኝ፡፡ መደንገጤ ምክንያቱ ገብቶት እየሳቀ “አይ [የልጅ ነገር] ላንተ ለካ አስር ዓመት ረዥም ነው” ብሎ አሾፈብኝ፡፡ እውነትም ግን ለእኔ አስር ዓመት ረዥም ነው፡፡ አስቡኝ እንግዲህ እኔ ገና ሀያን አልጨረስኩም  እሱ ደግሞ ሀምሳን ዘሏታል፡፡ አስር ዓመት ለእርሱ ቅርብ ከሆነች የእሱ ድሮ ለእኔ ጥንት ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ እርሱ ቅርብ ባላት አስር ዓመት ውስጥ እኔ ማትሪክ ዘጭ ብዬ፣ ራስታ ሆኜ፣ ስራ በደሞዝ ጀምሬ፣ ፍቅረኛ ይዤ፣ ፖለቲካ ጋዜጣ ማንበብ ጀምሬ፣ ቤት ተከራይቼ መኖር ጀምሬ፣ አንዴ ድንበር አቋርጬ. . . ምን አለፋችሁ ብዙ ነገር ሆኜ ነበር ስለዚህ እኔ እሱን ብሆን አስር ዓመትን ድሮ ነበር የምለው፡፡
በቀደም ዕለት ታድያ ታናሽ ወንድሜ ድሮ እያለ የዛሬ ሶስት አመቱን ታሪክ ሲያወራ አፌን ሸፍኜ ወይጉድ ከማለት ውጪ የድሮን ትርጉም ላብራራለት አልፈለግኩም፡፡ ምክንያቱም ድሮ ለሁላችንም የተለያ ነውና፡፡


(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ.ኮንጎ)

1 comment: