Tuesday, October 2, 2012

በየቀኑ መታጠብ ዋና አያስችልም


ፈረስ መጋለብ የጀመርኩ ዕለት እንዴት ፈርቼ እንደነበር ልነግራችሁ አልችልም ግን ዕድሜ ለሃይሌ ሩት ጎትጉቶ ለወሰደኝ እና ላስተማረኝ ብዙም ሳልቆይ ነበር ያለፍርሃት በፍጥነት መጋለብ የጀመርኩት፡፡ ወዳጄ ፍቅሩ ታድያ አዲስ አበባ ውስጥ ፈረስ መጋለቢያ/መማርያ/ ቦታ እንዳለ ስነግረው በደስታ ነበር የፈነጠዘው፡፡ ችግሩ ግን ጊዜ አግኝቶ ይዠው ለመሔድ አለመቻሌ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ረዳት አብራሪ በመሆኑ ጊዜ የለውም ቢሆንም አንድ እሁድ ጠዋት እንደምንም አመቻችቶ አያት ወደሚገኘው ባልደራስ የፈረስ ሜዳ ሔድን፡፡ ወዳጄ ለፈረስ አዲስ በመሆኑ ርዳታ እንደሚያስፈልገው እድሜ ጫን ላላቸው አለማማጅ ስነግራቸው ለሱ የምትስማማ ያሏትን “አስጎሪ” የተባለች ሴት ፈረስ አዘጋጁለት እና ልጓሟን ይዘው አሳፈሩት፡፡ የእኔ ስራ እነዚህን ሁለት ሰዎች ማገናኘት ነበር ፈረሰኛውን እና ካፕቴኑን፡፡ ፈረሰኛው ግልቢያ ከመጀመራቸው በፊት ግን ማብራርያ ቢጤ አደረጉለት “ . . . ፈረስ ማለት በአራቱም አቅጣጫ ገደል መሆኑን አትዘንጋ ድፍረት እና ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ፈረስ የጋላቢውን ልብ ማወቅ ይችላል መፍራትህን ካወቀ ከቁብም ሳይቆጥርህ ወደ ማደሪያው ይዞህ ይገባል፡”፡ ከመግለጫው በኋላ አስጎሪ እርምጃ ጀመረች ፈረሰኛውም ከፊት ከፊት ዱብ ዱብ እያሉ መሯቸው፡፡ ረዳት ካፕቴን ፍቅሩ ግን እንደጠበቀው ቀላል ሆኖ አላገኘውም ምኑም አልመሰጠውም ብዙህ ሺህ ጫማ ከፍብሎ ደመናን ሰንጥቆ ሲበር ያልፈራውን በመሬት እና በአስጎሪ ጀርባ መሃከል ያለው እርቀት አስፈራው፡፡  ስለዚህም ፍርሃቱን ሳይደብቅ ለሽማግሌው ፈረሰኛ ይነግራቸው ያዘ፡፡ በፍቅሩ መርበትበት ያልተደሰቱት ሽማግሌ ታድያ “አይ ኢንግዲህ አይዞህ ወንድ አይደለህ እንዴ ሰው እንኳን ይሔን ቀላሉን ፈረስ ቀርቶ አውሮፕላን ይነዳ የለ እንዴ” አሉት፡፡ ረ/ካ ፍቅሩ የሰማው ባለማመን እንዳፈጠጠባቸው “ኸረ እሱ ቀላል ነው” ብሎ ጮኸባቸው፡፡ የፈረሰኛው መልስ እኔን ራሱ በሳቅ አፈረሰኝ “እሱን እሱን እንኳን ተወው የማታውቀውን እንደሱ አትበል”፡፡
ከፈረሱ ከወረደ በኋላ እኔ ራሴ ለአለማማጁ ፈረሰኛ ይህ ሰው አውሮፕላን አብራሪ መሆኑል ላስረዳቸው ብሞክርም እየሳቅኩኝ ስለማወራላቸው ነው መሰለኝ አላመኑኝም፡፡ የመጀመርያው ቀን ባይሳካለትም ረ/ካ ፍቅሩ ጥሩ ፈረሰኛ ሆነ፡፡

እና ምን ይጠበስ አትሉኝም እናማ ለካ ደመናን እየዳሰሱ የማለፍ ፊዚክስ ፈረስ ለመጋለብ አይረዳም እላችኋለዋ፡፡ ደግሞ ባለፈው ለታ እንዲሁ እኔም የማልችለውን ዋና ለመዋኘት ስጣጣር አይቶኝ አንድ ተረተኛ ጓደኛዬ “ስማ እንጂ በየቀኑ ሻወር ስለምትወስድ ዋና የምትችል መሰለህ እንዴ” ብሎ ክንፌን የሰበረኝ እስካሁን እየጠዘጠዘኝ ነው፡፡

(ዲ.ሪ.ኮንጎ - ኪንሻሳ)

No comments:

Post a Comment