Friday, September 28, 2012

ስደተኛ ቃላት



አንድ ቀን አዲስ አበባ ከጋናዊው ወዳጄ ጋር መረቅ የሆነ ጨዋታ እየተጫወትን በየአይነት እየበላን ነበር፡፡ ምሳችን ቢያልቅም ጫወታችንን ላለማቋረጥ አብረን ወደ እጅ መታጠቢያው እየተሳሳቅን አመራን፡፡ እጄን ወደ ውሃው ሰንዝሬ እየተለቃለቅኩ ቀድመውን ከሚታጠቡት ሰዎች መሀል አንደኛውን ሳሙናውን እንዲያቀብለን ጠየቅኩትና ወደጨዋታዬ ልመለስ ስል ይህ ጋናዊ ወዳጄ በመገረም አይነት ሰውየውን ምን እንዳልኩት በእንግሊዝኛ ጠየቀኝ እኔም ሳሙናውን አቀብለኝ እንዳልኩት በአማርኛ ስነግረው በጣም ተደንቆ ሳሙና የሚለውን ቃል እንደሚያውቀውና እሱ ከመጣበት ጋና ውስጥ ያለ አንድ ብሔርም በተመሳሳይ ይህንን መታጠቢያ ሳሙና ብለው እንደሚጠሩት ነገረኝ፡፡
እንዴት ሳሙና የሚለው ቃል ከኢትዮጵያ ወደ ጋና ወይንም ከጋና ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ባላውቅም ከፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ እና አረብኛ ውጪ ከአፍሪካ ሀገራት ቋንቋዎች ጋር መተሳሰር ያለን አይመስለኝም ነበር፡፡ የኮንጎ ኪንሻሳ ኦፊሴላው ቋንቋ ፈረንሳይኛ ቢሆንም የሀገሬው ቋንቋ ሊንጋላ በሁለተኛነት ያገለግላል፡፡ በዚህ የመሀከለኛው አፍሪካ ቋንቋ ውስጥ ሁለት አስገራሚ ቃላት ገጥመውኛል፡፡ አንደኛው ኮታ የሚለው ሲሆን ትርጉሙ ከሀገሬ ኦሮምኛ ቃል ኮቱ ጋር አንድ አይነት ነው፡፡ ቃሉ ከኦሮምኛ ሊወሰድ እንደሚችል ግምት አለኝ ምክንያቱም ኦሮምኛ እንደ ስዋሂሊ ሁሉ በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ በብዙ ህዝብ የሚነገር ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ቃል ግን ፍፁም ልዩነት የሌለው እና በሰማሁት ቅፅበት ያስደነገጠኝ ነበር፡፡ በሰሜኑ የሀገሬ ክፍል ማይ ማለት ውሃ ማለት እንደሆነ አውቃለሁ ታድያ ይህ የትግርኛ ቃል እዚህ ኮንጎ ኪንሻ በሊንጋላ ቋንቋ ውስጥም ውሃ የሚለውን ትርጉም እንደያዘ እያገለገለ ይገኛል፡፡

እንዲሁ ደግሞ ሌላ ጊዜ በመሀከለኛው ምስራቅ ውስጥ የተሰራ አንድ የሆሊውድ ፊልም በግርጌ ፅሁፍ ታግዤ እያየሁ ሳለ ድንገት አንድ ቃል ጆሮዬን እንድጠራጠረው አደረገኝ:: ፊልሙን አቁሜ እንደገና ስሰማው ይህ አረብ ሰው “ፈትሸው” ሲል ሰማሁት የግርጌ ፅሁፉም ደግሞ “Search him” ይላል፡፡ ደግሜ ደጋግሜ ብሰማውም የሰማሁት በትክክለ “ፈትሸው” የሚል ነበር፡፡ ይህ ቃል ምንሊያደርግ እዚህ ፊልም ውስጥ እንደገባ አሁንም ድረስ አልገባኝም ምናልባት አረብኛ የሚችል ሰው ሊረዳኝ ይችላል፡፡
እስኪ በየሔዳችሁበት የገጠማችሁ ተመሳሳይ ነገር ካለ አካፍሉን፡፡

(ዲ.ሪ.ኮንጎ - ኪንሻሳ)

No comments:

Post a Comment