Friday, September 28, 2012

የመጀመርያ


(በውሸት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ዕውነተኛ ታሪክ)

ይህቺን ሚጢጢ ጥሁፍ እንድጥፋት የኮረኮረኝ ከባዱ ጦማሪ Naod ቤተሥላሴ በ “ናዖድ ኢትዮጵያዊ” ጦማሩ ላይ በአሜሪካ ሁሉ ነገር ‹‹የመጀመርያ› ባይሆንም በሚል ርዕስ አሜሪካኖች የመጀመሪያ ለመባል ትልልቅ ደንጊያዎችን እንዴት እንደሚያንከባልሉ ደስ በሚል ቋንቋ የገለፀውን ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ ናዖድ እንደገለፀው አሜሪካኖች ሩጫ ተወዳድሮ መጨረሻ ስለወጣ አሜሪካዊ ሯጭ ለመዘገብ መጀመርያአንደኛወይምየመጀመርያውየሚሆንበት መንገድ ይፈለግለታል፡፡ ከጥቂት ምርመራ በኋላ ወይ በዕድሜው፤ ወይ በጾታው፤ ወይ በትምህርት ደረጃው፤ ወይ በመጣበት ሀገር፤ ወይ መጨረሻ በወጣበት ሰዓት የመጀመሪያ ሰው እንደሆነ ሲረጋገጥ ‹‹በዚያ ሰዓት ለመግባት የመጀመርያው የሰባ ዓመት ዓዛውንት እንደሆነ ይዘገባል:: ታዲያ የናዖድን ፅሁፉን አንብቤ ስጨርስ ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም “በእኛ ቤት ታሪክ ውስጥ ሁለተኛ ልጅ በመሆን የመጀመሪያው ነኝ” ያለው ትዝ አለኝና ማሪኝ አሜሪካ አልኩ በልቤ::

ምንም ያህል አሜሪካኖቹ “የመጀመሪያ” መባልን ቢፈልጉም እንደ ኢትዮጵያዊ ግን የመጀመሪያ የሚለውን ቃል አብዝቶ የሚጠቀም ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ በተለይ እነዚያ የፈረንጅ አገር በረዶ ቀምሰው የሚመጡ Die-Ass-‹ፖራዎች እኛን የሀገርቤት ሰዎች ለማሞኘት ይህችኑ ቃል እንደሚጠቀሙበት አውቃለሁ (አሞኝተውን ሞተዋል)፡፡ “ . . .ይገርምሀል ይህን ሀሳብ (idea) ለመጀመርያ ጊዜ ለዚህ ሀገር ያስተዋወቅኩት እኔ ነኝ፣ የአገጭ ጢምን በተመለከተ ለመጀመርያ ጊዜ ጥናታዊ ፅሁፍ የሰራሁት እኔ ነኝ፡፡ ቱቦ የሚለውን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋልኩት እኔ ነኝ::” ብቻ ምናለፋችሁ የማይባል የለም (በነገራችን ላይ ለነዚህ ዳይአስፖራዎች አፌን ሾል አድርጌ ወደቀኝ ጠምዝዤላቸዋለው)፡፡

ባለፈው አንዱ Die-Ass-‹ፖራ ምን ይለኛል “ሬይ ባን” የተባለውን ውድ መነፅር በማድረግ ከሀበሻ ዘር ፈር ቀዳጅ ነኝ ብሎ ወሬውን በሁለት ጉንጩ ሞልቶ ሲያወራ እኔስ ምኔ ሞኙ በጣቴ የአፌንጥግ እየነካካሁ እዝች ጋ የሆነች ነገር አለችብህ ጥረጋት አልኩት እፍር እንደማለት ብሎ አፉን በገዛ መዳፉ እየሞዠቀ “ውይ በናትህ ምንድነው ያለብኝ” ሲለኝ ፈጠን ብዬ “ወሬ፣ ወሬ አለብህ” አልኩታ ይሞታል እንዴ ታድያ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ድንበር ስለተሻገሩ ብቻ ካልተሻገርነው በላይ የመጠቁ የሚመስላቸው ነፍ ናቸው (nuff - ብዙ)፡፡ የጥርስ ክሊኒክ ውስጥ የሚሰራው ወዳጄ ባለፈው ከዶክተሯ ጋር ሲጨዋወቱ በወሬያቸው መሀል “እኔ ማለት” አለችው “እኔ ማለት ጥርሷን በብረት አጥር (Orthodentic) ያሳጠረች የመጀመርያዋ አፍሪካዊ ከመሆኔ ባሻገር ለመጀመርያ ጊዜ ከኢትዮጵያ በሞያሌ በኩል ወደኬንያ የመኮብለልን መንገድ የቀደድኩት ሰው ነኝ ብላው እርፍ፡፡ ቆይ እንደው እውነትስ ቢሆን ይወራል እንዴ ይሄ? ጥርሷን ማሳጠሩንስ ታሳጥረው ግን ኬንያ ጠረፍ አካባቢ ያሉት የዱር እንስሳት ስለ ድንበር ቀደዳው ቢሰሙ አፋቸውን ሾል አድርገው ወደቀኝ አይጠመዝዙባትም? 

እኔ የ14 አመት ልጅ እያለሁ አንድ ቆንጆ ጫማ እንደተገዛልኝ አስታውሳለሁ፡፡ የሆነ ቢጫ መስመር ዲዛይን ያለው እና በጣም ከማማሩ የተነሳ እንደዚህ አይነት ጫማ ማንም አድርጎ እንደማያውቅ እርግጠኛ ሆንኩ (ከሰሃራ በታች ቢጫ መስመር ያለው ነጭ ጫማ በማድረግ የመጀመርያው እንደሆንኩ ተሰማኝ)፡፡ በነጋታው በዚያ ለእኔ ብቻ በተሰራ ጫማ ቀስ እያልኩ እየረገጥኩ ስሔድ ስሜቴን የጎዳ ትዕይንት ተመለከትሁ ሁለት የላይ ሰፈር ልጆች ራሱን የእኔን የሚመስል ጫማ አድርገው ኳስ ይራገጣሉ፡፡ አላመንኩም፣ እንባ እንባ እያለኝ ወደቤት ተመለስኩ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታድያ ከአምስት ያላነሱ የእኔ አይነት ጫማዎች አየሁኝ ያውም ያረጁ፡፡ ወዲያውኑ ከሰሃራ በታች የሚለውን ትቼ ክልሉን የቤታችንን ግድግዳ አደረግሁት፡፡ (ለነገሩ አሁንም አልፎ አልፎ እንዲህ አይነቱ ነገር ውልብ ይልብኛል)፡፡  

እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉ እኔም በ”ታላቋ” አሜሪካ የምትኖር ዘመድ(አክስት) አለችኝ፡፡ ትክ ብዬ የአክስቴን ፊት ስመለከት የእድሜ ጎማ ምን ያህል ጥርስ የበዛበት እንደሆነ እያስተዋልኩ እቆዝማለሁ፡፡ ታዲያ እርሷም በተመሳሳይ ቫይረስ በመጠቃቷ ኮሎምበስ እንኳን ጉራ ይሆንብኛል ብሎ ያልተናገረውን “የአሜሪካንን መሬት ለመርገጥ የመጀመሪያው ነኝ” አይነት ቃና ያለው ንግግር ታበዛለች፡፡ እንደውም ረስቼው ይሁን ተምታቶብኝ ባላውቅም “አሜሪካን ሀገር ስሔድ እኔና ኩንታኩንቴ ብቻ ነበርን ጥቁሮች” ሳትለኝ አትቀርም (ባትለኝም ብላኛለች) ፡፡

ይህ አይን ያወጣ ውሸት(ፉገራ) ከቤት ተራምዶ ወጥቶ በየድርጅቱ ሁሉ መስፋፋቱን ደግሞ ለማወቅ ኢቲቪን ለ 3 ደቂቃ ያህል “ሳይታክቱ” መመልከት ይበቃል፡፡ “በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የፕላስቲክ ጆግ ማምረቻ ከፈትን”፣ “የመጀመርያው የጤፍ እንጀራ ጋገርን . . .” አይነት ማስታወቂያ/ዜና መስማት በጣም የተለመደ ሆኗል፡፡

ግን እውነት እውነቱን እናውራ ከተባለ እኮ ኢትዮጵያ ማለት ቅኝ ያልተገዛች የመጀመርያዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ በኦሎምፒክ የመጀመርያውን ወርቅ ያገኘች የመጀመርያዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ የራሷ ፊደላት ያላት የመጀመርያዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ እስልምናን ከመካከለኛው ምስራቅ በፊት ክርስትናንም ከአውሮፓውያን በፊት በመቀበል የመጀመርያዋ ሀገር፣ በመፅሀፍ ቅዱስ እና በቅዱስ ቁርዓን ላይ ከ50 ጊዜ በላይ ስሟ የተጠቀሰ የመጀመርያዋ አፍሪካዊት/አለማቀፋዊት/ ሀገር፣ ሰው የሚባለው ፍጡር /ምናልባትም አዳም/ የተፈጠረባት የመጀመርያዋ ሀገር፣ ቡናን ለአለም ያበረከተች የመጀመርያዋ ሀገር፣ ቀድማ የነቃች የመጀመርያዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ ቀድማ ያንቀላፋች የመጀመርያዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ . . . እናንተዬ ለካ የእውነትም በሁሉም የመጀመርያ ነን?

ለነገሩ እኔ ራሴ ስለዚህ ጉዳይ ለማውራት እጅን ከኪቦርድ በማገናኘት ከ ናዖድ ቀጥሎ የመጀመርያው ሰው ነኝ፡፡

(ኪንሻሳ - ዲ.ሪ.ኮንጎ)

2 comments:

  1. "በውሸት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ዕውነተኛ ታሪክ"
    lol....

    ReplyDelete
  2. youare good look

    ReplyDelete