ስደተኛ ቃላት
አንድ ቀን አዲስ አበባ ከጋናዊው ወዳጄ ጋር መረቅ የሆነ ጨዋታ እየተጫወትን በየአይነት እየበላን ነበር፡፡ ምሳችን ቢያልቅም ጫወታችንን ላለማቋረጥ አብረን ወደ እጅ መታጠቢያው እየተሳሳቅን አመራን፡፡ እጄን ወደ ውሃው ሰንዝሬ እየተለቃለቅኩ ቀድመውን ከሚታጠቡት ሰዎች መሀል አንደኛውን ሳሙናውን እንዲያቀብለን ጠየቅኩትና ወደጨዋታዬ ልመለስ ስል ይህ ጋናዊ ወዳጄ በመገረም አይነት ሰውየውን ምን እንዳልኩት በእንግሊዝኛ ጠየቀኝ እኔም ሳሙናውን አቀብለኝ እንዳልኩት በአማርኛ ስነግረው በጣም ተደንቆ ሳሙና የሚለውን ቃል እንደሚያውቀውና እሱ ከመጣበት ጋና ውስጥ ያለ አንድ ብሔርም በተመሳሳይ ይህንን መታጠቢያ ሳሙና ብለው እንደሚጠሩት ነገረኝ፡፡